የህፃናት መንዘፍዘፍ / እንፍርፍሪት

የህፃናት መንዘፍዘፍ / የሚጥል በሽታ

በተለምዶ የሚጥል በሽታ፣ እንፍርፍሪት ወይም መንዘፍዘፍ የምንለው የጤና ምልክት በህፃናትም ላይ ይከሰታል። መንዘፍዘፍ የምንለው ልጆች ከተለመደው እንቅስቃሴያቸው ውጭ ከቁጥጥር የወጣ የሰውነት መገተርና መንቀጥቀጥ በሚያሳዩበት ጊዜ ነው። ተያይዞም ራስን መሳትና የሰውነት መድከም ሊታይባቸው ይችላል።

ይህም የሚከሰተው ጤናማ ያልሆነ እና ከመጠን በላይ የሆነ በአንጎል ነርቮች መካከል የሚፈጠር የኤሌክትሪክ ስርጭት ሲኖር ነው።  የህፃናት እንፍርፍሪት (መንዘፍዘፍ) ከ24 ሰአት ባለፈ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በሚከሰትበት ወቅት የሚጥል በሽታ ወይም ኤፕለፕሲ (Epilepsy) እንለዋለን። ሁሉም የህፃናት እንፍርፍሪት (መንዘፍዘፍ) ወደ የሚጥል በሽታ አያድግም። የህፃናት እንፍርፊሪትም ሆነ የሚጥል በሽታ በማህበረሰባችን እንደሚታሰበው የመጥፎ እርግማን ምልክቶች አይደሉም። በሚከሰቱበት ጊዜም ወደ ጤና ባለሙያ በመሄድ  በህክምና መቆጣጠር ይቻላል። ተገቢውን ክትትል በማድረግም ህፃናትና ልጆች ጤናማ አስተዳደግ እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል።

 

ለህፃናት እንፍርፍሪት መከሰት መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?

የህፃናት እንፍርፍሪት በብዙ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል። እነዚህም ምክንያቶች ቅድመ ወሊድ፣በወሊድ ወቅት ወይም ድህረ ወሊድ  የተከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ። እስቲ መንስኤዎቹን አብረን እንመልከታቸው

  • ምክንያት የለሸ ወይም መንስኤው ያልታወቀ
  • በዘር የሚተላለፍ
  • ተፈጥሮአዊ አፈጣጠር ወይም ከውልደት ጊዜ ጀምሮ የሚኖር
  • በእርግዝና ጊዜ አስፈላጊ የቅድመ-ወሊድ ክትትል ካለማድረግ እና ፅንሱን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች አለማወቅ
  • በእርግዝና ወይም በወሊድ ጊዜ በማህፀን ውስጥ የነበረ መታፈን
  • ከፍተኛ የሆነ የህፃናት ትኩሳት
  • የሰውነት ስኳር መጠን ከልክ ማነስ ወይም መብዛት
  • የሰውነት ንጥረነገሮች መዛባት
  • ተፈጥሮአዊም ሆነ ከውልደት በኃላ የሚመጣ የልብ በሽታ
  • የማጅራት ገትር በሽታ፣ አንጎላችንን የሚያጠቁ በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መያዝ(ወባ፣ የአንጎል ሳንባ ነቀርሳ)
  • የአንጎል መግል መያዝ እና እብጠት፣ የአንጎል ዕጢ መኖር
  • መርዛማ ነገሮች ወደ ሰውነታችን መግባት
  • የአንጎላችን የደም ዝውውር መስተጓጎል፣ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ
  • በጭንቅላት ላይ የደረሰ አካላዊ ጉዳት

ከላይ ከተጠቀሱት መንስኤዎች ውስጥ በአብዛኛው ለህፃናት እንፍርፊሪት መንስኤ ሆኖ የሚገኘው በህፃናት ላይ የሚከሰት ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት ነው። ይህም ከ6 ወር ህፃናት ጀምሮ እስከ 6 አመት በሚገኙ የልጆች እድሜ ክልል ውስጥ  ከ2-5% ባሉት ላይ ይከሰታል።  በአጠቃላይ ሲታይ አብዛኛው የህፃናት እንፍርፊሪት በሚያድጉበት ጊዜ የሚተዋቸው አይነት ነው። በእድገታቸውም ላይ የከፋ ጉዳት አያስከትልም። ነገር ግን መንስኤውንና አይነቱን ለይቶ ለማወቅ ህፃናትን ወደ ጤና ተቋም ወስዶ አስፈላጊውን ምርመራ እና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

 

የህፃናት እንፍርፊሪት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የህፃናት እንፍርፍሪት ምልክቶችን ለይቶ ማወቅ አስፈላጊውን የመጀመሪያ እርዳታ ለመስጠትና በቶሎ ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ ይጠቅማል። እስቲ የህፃናት እንፍርፊሪት ምልክቶችን እንያቸው፣

  • የሰውነት መገተር፣መወራጨት፣መንዘፍዘፍ እና መንቀጥቀጥ
  • ያልተለመደ የአይንና የከንፈር እንቅስቃሴዎች ፣ የምራቅ መዝረብረብ
  • ራስን መሣት፣ የሰውነት መድከም
  • በድንገት ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ መውደቅ
  • ለተወሰኑ ደቂቃዎች ወይም ሰዓታት መፍዘዝ፣ መደንዘዝ  ( አደግ ባሉ ህፃናት ላይ)
  • ሽንትና ሰገራ በሰውነት ላይ መልቀቅ
  • ተያያዥ የሆነ የአተነፋፈስ እና የልብ ምት ለውጥ

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከ 5 ደቂቃ በላይ ከቆዩ ወይም ደግሞ ህፃናት በደቂቃዎች ልዩነት ያለምንም መሻሻል  እነዚህን ምልክቶች በተደጋጋሚ እያሳዩ ከሆነ የከፋ አደጋ መኖሩን አመላካቾች ናቸው። ስለሆነም ምልክቶቹን ከሚያሳዩበት ቅፅበት ጀምሮ ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ መፋጠን አለብን።

 

ህፃናት በሚንቀጠቀጡበት ጊዜ ምን ማድረግ አለብን?

በመጀመሪያ ማንኛውንም እርዳታ ከመስጠታችን በፊት ራሳችንን ማረጋጋት አለብን። ከላይ በፅሁፍ እንደተጠቀሰው አብዛኛው የህፃናት እንፍርፍሪት በራሱ የሚቆምና የሚተዋቸው አይነት ነው። ራሳችንን ከተቆጣጠርን በኃላ ወዲያውኑ ከአከባቢያቸው ሊጎድዋቸው የሚችሉትን ዕቃዎች ማራቅ አለብን። በተጨማሪም በሚወራጩበት ጊዜ ጭንቅላታቸው እንዳይጎዳ ከራሳቸው ስር ትራስ ወይም ለስለስ ያለ መደገፊያ ማድረግ አስፈላጊ   ሌላው አፋቸው ውሰጥ ምንም አይነት ነገር መኖር ወይም መግባት የለበትም። እንዲሁም የክብሪት ጭስ ማሽተትና ሌሎች የመሳሰሉ አጉል ልምዶችን በፍፁም መሞከር የለብንም።ሰውነታቸው በሚንቀጠቀጥ ጊዜ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን አፍኖ መያዝ አያስፈልግም። ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ከሆነ  ደግሞ ንፁህ አየር እንዲንሸራሸር መንገድ እንዲከፍቱ ማሳሰብ ያስፈልጋል። ህፃናት ከፍተኛ ትኩሳት ካላቸው ንፁህ ጨርቅ በውሃ በመንከር ግንባራቸው ላይ ማድረግ፣ ደራርበው የለበሱት ልብስ ካለም ማውለቅ የሰውነታቸው ሙቀት እንዲቀንስ ይረዳል። ከዚህ ሌላ ሰዓት መያዝና እንፍርፊሪቱ ለስንት ደቂቃዎች እንደቆየ ማወቅ ለጤና ባለሙያዎች ስለመንስኤው ጥሩ መረጃ ስለሚሰጥ ሰዓት መያዝ መልካም ነው። እንፍርፍሪቱ ካቆመ በኃላ ህፃናት ከጀርባቸው ይልቅ በጎናቸው እንዲሆኑ ( ከላይ በስዕሉ እንዳለው)ሰውነታቸውን መደገፍ ይጠቅማል። ይህም ትውከት ወይም ቃር ቢኖር ወደ ሳንባቸው እንዳይገባ ይረዳል።

 

የህፃናት እንፍርፊሪት በጤና ተቋማት እንዴት ይታከማል?

ህፃናት ወደ ጤና ተቋም ከደረሱ በኃላ እንደአስፈላጊነቱ ኦክስጂን ላይ ሊደረጉ ይችላሉ። አካላዊ የሰውነት ምርመራ ከነርቭ ምርመራ ጋር ይደረጋል። የደም እና የስኳር፣ የንጥረ ነገሮች እና የተለያዩ የሰውነት አካላት (የልብ፣ የኩላሊት ወዘተ…) ተግባር ምርመራ ይደረግላቸዋል። ትኩሳት ካላቸው ከጀርባቸው ወገብ ላይ የመቅኔ ፈሳሽ በመውሰድ ምርምራ ሊደረግ ይችላል። የአንጎል ሲቲ ስካን እና ኤምአርአይ ሊታዘዝ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ኢኢጂ በተባለ መሣሪያ ሊታዩ ይችላሉ። ይህ መሣሪያ የአንጎልን የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ በመለካት የሚጥል በሽታ አይነቱን ለመለየት ይጠቅማል።

 

የህፃናትን እንፍርፍሪት ለመከላከል ምን ማድረግ አለብን?

  • በጤና ባለሙያ እንደታዘዘው አስፈላጊ የሆነ ክትትል በጤና ተቋማት ማድረግ
  • የታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣ያለ ጤና ባለሙያ ትዕዛዝ መድሃኒት አለማቋረጥ እንዲሁም ያልታዘዙ መድሃኒቶችን አለመውሰድ
  • በእርግዝና ወቅት እናቶች አስፈላጊውን ቅድመ ክትትል ማድረግ፣ በባለሙያ የሚታዘዙ ምርመራዎችን ማድረግ፣ ክትባትና መድሃኒቶችን መውሰድ እንዲሁም ፅንሱን ሊጎዱ ከሚችሉ ከአልኮል፣ሲጋራ እና አደንዛዥ ዕፆች መታቀብ
  • ህፃናት አስፈላጊውን የተላላፊ በሽታዎች ክትባት በወቅቱ በጤና ተቋማት እንዲያገኙ ማድረግ
  • ህፃናት ከፍተኛ ትኩሳት በሚኖራቸው ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ

እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ የህፃናትን እንፍርፊሪት ለመቆጣጠር እና ህፃናት ጤናማ አስተዳደግ እንዲኖራቸው ለማድረግ ትልቅ አስተዎፅዖ ይኖረዋል።

 

ማጣቀሻ