የማህፀን በር/ጫፍ ካንሰር መከላከልያ መንገዶች

በዶ/ር ፍሥሓ ጓዴ -ደ/ታቦር ዩኒቨርስቲ ሕክምና ትምህርት ቤት (Medical Intern)
አርትኦት  እና እርማት- በዶ/ር ቅድስት ገፃድቅ (Obstetrician and gynecologist)

Levels of prevention (የመከላከል ደረጃዎች)

፩. የመጀመሪያ ደረጃ መከላከል (primary level of prevention)

ይኽ ክፍል እንደዋነኛ መርህ ብሎ የሚይዘው “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚል ሲኾን የካንሰር በሽታው ከመከሰቱ በፊት መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ያጠቃልላል።

  1. የሥነ ባሕርይ ለውጥ (behavioural):- እንደሚታወቀው የማህፀን ጫፍ ካንሰር 90% በላይ የሚኾነው የሚተላለፈው Human Papilloma Virus(HPV) በተሰኙ የአባላዘር በሽታ አምጪ ቫይረሶች ስለኾነ አጋላጭ የግብረ ስጋ ግንኙነቶችን ማስወገድ ትልቁ አንኳር ጉዳይ ነው። ይኸውም 3ቱ የ”መ” ሕጎች ወይንም “ABCs” የምንላቸውን መከላከያ መንገዶች ያጠቃልላል።

✔️ መታቀብ (Abstainence)- በተለይ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ከ16 ዓመት በፊት የሚደረግ ግንኙነት እንዲሁም በእድሜ ከገፉ ወንዶች ጋር የሚኖር ግንኙነት የተጋላጭነት ዕድልን የሚጨምሩ ናቸውና።

✔️ መወሰን (Be faithful)- በታማኝነት ላይ የተመሰረተ የመጀመሪያውን አንስቶ አንድ ባል ለአንዲት ሚስት ብቻ የሚኖር ግንኙነት ከኾነ ተጋላጭነትን እጅግም ይቀንሰዋል።

🥉መጠቀም (Condom):- ይኽ መንገድ እንኳ እንዲያ ከመቅረት የገንፎ እንጨት መላስ እንዲሉት አይነት ቢኾንም እንኳ የላይኞቹ መንገዶች ካልተሳኩ ይኸውም ይመከራል(ግን 100% ይከላከላል ማለት አይደለም።)

  1.  መከትብ (vaccination):- ሳይንስ ከደረሰባቸውና ካንሰርን በክትባት መልክ መከላከያ መንገዶች ያሉት ይኸው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ዋነኛው ሲኾን ክትባቱ ግን የሚሰጠው ከ9-14 ዓመት ለኾናቸውና ግንኙነት ላልጀመሩ ልጃገረዶች እንዲኾን ይመከራል።

የክትባቱ ትልቁ ጥቅም የHPV ኢንፌክሽን እንዳያጠቃና ኤንፌክሽኑ ገና ቀድሞ ወደ ካንሰርነት ደረጃ እንዳይቀር እንጂ በካንሰርነት ደረጃ ላይ ለደረሰ ሕመም ምንም ፋይዳ የለውም፤ HPV positive የኾነውን ወደ HPV negative በፍፁም አይቀየርም።

የኤችፒቪ ቫይረስ (HPV) መከላከያ ክትባት የተለያዩ አይነቶች ያሉት ሲኾን በእኛ ሃገርም እየተሰጠ ይገኛል። የመከላከል ብቃቱ ደግሞ ከ80-90% በላይ ውጤታማ ይደርሳል።

፪. ኹለተኛ ደረጃ መከላከል (Secondary level of prevention)

ይኸኛው ደግሞ ቅደመ ካንሰር የምርመራ ሂደት (precancerous lesions screening and treatment) ተብሎ የሚጠራም ሲኾን ዋነኛ ዓላማው ደግሞ አንድ የኤችፒቪ ቫይረስ (HPV) ኢንፌክሽን ወደ ካንሰርነት ደረጃ ለመሸጋገር በትንሹ 10-15 ሊወስድ ይችላልና በዚህ መካከል የሚታዩትን ለውጦች አስከፊ ደረጃዎች ላይ ሳይደርስ የሚደረጉ ምርመራዎችን እና ወዲያውኑም የሚወሰዱትን የሕክምና እርምጃዎችን ያጠቃልላል።

ይኽ መርህ ደግሞ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መታከም” የሚል አንድምታ አለው።

በዚህም መሰረት የተለያዩ ምርመራዎችን ማሰራትና በዚሁ ተነስቶ የሚወሰዱ ሕክምናዎች ያሉት ሲኾን በእኛም ሀገር  እየተሰራበት ይገኛል።

ለማየት ያክል:-

  1. የፓፕ ምርመራ (pap smear):- ይኽ የምርመራ አይነት ከማህፀን ጫፍ (cervix) ላይ ናሙና በመውሰድ በአጉሊ መነጽር (Microscope) በመታገዝ የሥነደዌ ሕክምና እስፔሻሊስት(pathologist) የካንሰር ሴሎች አለመኖራቸውን የሚያረጋግጥበት መንገድ ሲኾን ከ21-65 ዓመት ላሉ ሴቶች በየ አምስት ዓመቱ ይሰራል። በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ ላለባቸው ግን የግብረስጋ ግንኙነት ከጀመሩ አንስቶ በየዓመቱ ሊደረግ ይችላል።

–> Pap smear በኛ ሀገር የሚሰራ ቢኾንም ከዋጋው ወደድ ማለት እና የዘርፉን ባለሙያዎችንም ከማስፈለጉም አንፃር በሁሉም ቦታ አይገኝም።

  1. VIA/VILI ( visual inspection with asectic acid or lugols iodine)፦ እነኚህ የምርመራ አይነቶች ደግሞ በቀላሉ የሚገኙና እምብዛም ያልተወሳሰቡ ስለኾኑ በየትኛውም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ጨምሮ በቀላሉ የሚገኙ ሲኾን ችግር ከተገኘ ወዲያውኑም ማየት አብሮ ማከም በሚል መርህ ይከወናሉ።

ይኽ ደግሞ የሚሰራላቸው ሴቶች ከ30-49 ዓመት ያሉት ነው።

የሕክምናው አይነቶች የተለያዩ አይነቶች ኾነው:- በቅዝቃዜ (cryotherapy)፣ ሙቀት (laser ablation) እንዲኹም ደግሞ በቀዶ ሕክምና ቆርጦ ማውጣት (LEEP, conization,… )የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።

፫. ሦስተኛ ደረጃ መከላከል (Tertiary Level of prevention)

ይኸኛው ደረጃ ደግሞ በሽታው የካንሰር ደረጃ ከደረሰ በኋላ የሚወሰዱትን እርምጃዎች ማለትም FIGO-Staging በተሰኘ የሕክምና የማህፀን ጫፍ ካንሰር ክፍፍልን መሰረት በማድረግ ወደ አራት ዋና ክፍሎች (stage-I, II, III, IV) ተብሎ ከተሰጠው በኋላ እንደገና ንዑስ ክፍሎችን በ a,b c እየተደረገ በዘርፉ ባለሙያዎች የሚወሰን ኾኖ እንደየኹኔታው በቀዶ ሕክምና (surgery)፣ በጨረር (radiation therapy)፣ በካንሰር መድኃኒት (chemotherapy) አማካኝነት ለየብቻ ወይንም ኹሉንም በአንድ ጊዜ እየተደረገ ከደረጃ (Stage) 1-3 ያሉት የሚታከሙበት መንገድ እንደየኹኔታው ያለ ሲኾን ለመጨረሻው ደረጃ (stage-4) ከደረሰ ግን የድጋፍና በርህራሄ ማገዝ ሕክምና (supportive and palliative Care) ሕክምና ዘዴዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል።