የማህፀን በር/ጫፍ ካንሰር

በዶ/ር ፍሥሓ ጓዴ -ደ/ታቦር ዩኒቨርስቲ ሕክምና ትምህርት ቤት (Medical Intern)
አርትኦት  እና እርማት- በዶ/ር ቅድስት ገፃድቅ (Obstetrician and gynecologist)

የማህፀን በር/ጫፍ ካንሰር ምንድነው?

የማህጸን በር (Cervix) የማህፀን የታችኛው ክፍል ነው፤ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የሚከሰተው ደግሞ እዚሁ አካባቢ ያሉ መደበኛ ህዋሶች ወደ ያልተለመዱ ህዋሳት ሲቀየሩ   እና ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ሲያድጉ (neoplastic) ነው።

የማህፀን በር ካንሰር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የማህፀን በር ካንሰር መጀመሪያ ላይ በደንብ እስኪያድግ ድረስ ምንም አይነት ምልክትን ላያሳይ ይችላል።

ምልክቶችን በሚያመጣበት ጊዜ ግን:-

– በወር አበባ ዑደቶች መካከል ጊዜውን ሳይጠብቅ ደም መፍሰስ (Intermenstrual bleeding)

– ከወሲብ በኋላ መድማት (postcoital/contact)

– ከማረጥ በኋላ መድማት (postmenopausal bleeding)

-በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ህመም(dyspareunia)

– የማህፀን ፈሳሽ (vaginal discharge)

– ሽንትን ለመሽናት መቸገር

– ወደ ቋተ ኩስ (rectum &anal canal) ስለሚሰራጭ በፊንጢጣ በኩል  መድማት ፣ ለመፀዳዳት መቸገር

– እንዲኹም ወደተለያዩ የአካል ክፍሎች በመሰራጨት እንደየ ቦታዎቹ ልዩ ልዩ ምልክቶች ሊኖሩት ይችላሉ።

እነዚህ ምልክቶች ካንሰር ባልሆኑ ሁኔታዎችም ሊከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በአብዛኛው እድሜ እየገፋ በሚሄደበት ወቅት ከኾነ ግን ካንሰር የመሆን እድሉ እየሰፋ ስለሚሄድ ከብልትዎ ደም መፍሰስ ካለብዎ ለሐኪምዎ ይንገሩ፤ የሕክምና ክትትልም ያሻዎታልና።

 የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ አለን?

አዎ፦ የማህፀን ጫፍ ህዋስ ምርመራ (“የፓፕ ስሚር (pap smear)” ተብሎም ይጠራል) ሴቶችን የማኅጸን በር ካንሰርን ለመመርመር ይጠቅማል።

በኢትዮጵያ ውስጥም እንደ ቪአይኤ (VIA) እና የሉጎልስ አዮዲን ምርመራን ጨምሮ የተለመዱ እና ብዙም ወጭ የማያስወጡ (ያልተወሳሰቡ) በቀላሉ የሚደረጉ ምርመራዎች አሉ።

ከላይ ያሉትን የምርመራ ውጤት ያልተለመደ(abnormal) ከሆነ ፤ ዶክተሩ ባዮፕሲ(Biopsy) ተብሎ የሚጠራውን ምርመራ ሊያሰራልዎት ይችላል። ባዮፕሲ (Biopsy) ወይም የናሙና ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ የማኅጸን ጫፍን በተሻለ ሁኔታ ለማየት ሐኪሙ  “ኮልፖስኮፕ(colposcope)” የተባለ አጉሊ መነጽርን በመጠቀም ሊያይልዎት ይችላል።

 

የማህፀን በር ካንሰር እንዴት ይታከማል?

የማህፀን በር ካንሰር በተለያዩ መንገዶች ሊታከም የሚችል ሲሆን  ትክክለኛው የህክምና አማራጭ በካንሰሩ ደረጃ፣ በእድሜዎ፣ በሌሎችም የጤና ችግሮች እና  ወደፊት ለማርገዝ ፍላጎቶ ላይም ታይቶ የሚወሰን ይሆናል። የህክምና አማራጮች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-

  • ቀዶ ጥገና (Surgery)
  •  የጨረር ሕክምና (Radiation therapy) – ጨረር የካንሰር ሕዋሳትን ይገድላል።
  • የመድኃኒት (chemotherapy)– ኪሞቴራፒ የካንሰር ሕዋሳትን የሚገድሉ ወይም እድገታቸውን የሚያቆሙ መድኃኒቶች የሕክምና ቃል ነው።

 

አንድ ቀን ማርገዝ ብፈልግስ?

  • አንድ ቀን ልጅ ለመውለድ ከፈለጉ፣ ህክምና ከመደረጉ በፊት ከሐኪምዎ ጋር ይነጋገሩ። አንዳንድ ሴቶች የማህጸን ካንሰር ከታከሙ በኋላ ማርገዝ የሚችሉበት አማራጮች ሊኖር ስለሚችል።
  • ነገር ግን አንዲት ሴት እንደ የማህፀን ቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምና፣ ወይም አንዳንድ የኬሞቴራፒዎች የሕክምና አማራጮች በኋላ ማርገዝ አትችልም።
  • አብዛኛውን ጊዜ ለማርገዝ መሞከር ከመጀመራቸው በፊት ከ 6 እስከ 12 ወራት መጠበቅ አለባቸው፤ ምክንያቱም ሰውነታቸው ለመፈወስ ጊዜ ይፈልጋልና።

ከህክምናው በኋላ ምን ይሆናል?

  •  ከህክምናው በኋላ፣ ካንሰሩ ተመልሶ እንደመጣ ለማወቅ በየጊዜው ምርመራ ይደረግልዎታል። የክትትል ምርመራዎችን የማህጸን አካላዊ ህዋስ ምርመራዎችን ጨምሮ ሌሎች የራጅና የውስብስብ የምርመራ ምስሎችን (advanced imaging modalities) መነሳትን ሊያካትት ይችላል።
  •  ካንሰሩ ተመልሶ ከመጣ ወይም ከተዛመተ ተጨማሪ ቀዶ ጥገና፣ ጨረር ወይም ኬሞቴራፒ (radiotherapy and/or chemotherapy) ማግኘት ሊኖርብዎት ይችላል።

 

የማህፀን በር ካንሰርን መከላከል ይቻላልን?

አዎን! ያውም በብዙ ሁኔታዎች ነዋ! በደንብ ኾኖ ይቻላል።

ከሞላ ጎደል ሁሉም የማኅጸን ጫፍ ካንሰር የሚከሰተው HPV ተብሎ በሚታወቀው የአባላዘር በሽታ (Sexual transmitted infections) ቫይረስ አማካኝነት ነው።

ስለሆነም ለዚህ ቫይረስ በክትባት መከላከል ስለሚቻል በሚመከርበት ጊዜው ከወሰዱ መልካም ውጤት አለው።

ይህ ክትባት ለወንዶች እና ለሴቶች ይሰጣል፤ እናም አንድ ሰው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ከመጀመሩ በፊት ከወሰደው በተሻለ ሁኔታ ይሠራለታል።

እንዲሁም የቅድመ ካንሰር ህዋሶች (Precancerous lesions)ን ማከም ወደ የማህፀን በር ካንሰር እንዳይቀየሩ ያደርጋል።

ሌላኛውም ደግሞ አጋላጭ ምክንያቶችን (Risk factors) ለማየት ያክል  የሚከተሉትን ኹኔታዎች እንደሆኑ ጥናቶች ይጠቁማሉና  ማስተካከል የሚቻሉትን በጊዜው እርምጃ መውሰድ በጣም ወሳኝ ነው:-

– በመጀመሪያ የግብረ ሥጋ ግንኙነት (<16 ዓመታት) ፣

– ብዙ የወሲብ አጋሮች (multiple sexual partners)፣

– ሲጋራ ማጨስ (smoking)

– የባልየው የቀድሞ ሚስት በማህፀን ጫፍ ካንሰር የተጠቃች/የሞተች መኾን (dangerous husband theory ተብሎ ይታወቃል፤ ምክንያቱም ሰውየው HPV የሚባለው ቫይረሱ ስለሚኖርበትና ለአዲሲቷ ሚስቱ ስለሚያስተላልፍ ነው።)

– ዘር (hereditary/genetics)

– የኤችአይቪ በሽታ (WHO stage IV HIV/AIDS defining illness)፣

– ብዙ መውለድ(High parity)

– ዝቅተኛ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ደረጃ (Low socioeconomic status) ይኸውም ቅደም ካንሰር ምርመራዎችን ጨምሮ ሌሎቹን ለማድረግ አቅም ስለማይፈቅላቸው ነው።

ሌላ ምን ማድረግ አለብኝ?

ስለ ክትትልዎ እና ምርመራዎችዎ ሁሉንም የዶክተርዎን መመሪያዎች መከተል አስፈላጊ ነው።

በተጨማሪም በህክምና ወቅት ስለሚያጋጥሙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ወይም ችግሮች ከሐኪምዎ ጋር  መነጋገር አጅጉን አስፈላጊ ነው።

ኹልጊዜም ስለሕክምናዎና ምን እንደሚስማማዎት ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎችን እነኚህን በመጠየቅ ይወቁ፡-

1. የዚህ ሕክምና ጥቅሞች ምንድን ናቸው? ረጅም ዕድሜ እንድኖር ሊረዳኝ ይችላል? ምልክቶችን ይቀንሳል ወይስ ይከላከላል?

2. የዚህ ሕክምና ጉዳቶች ምንድናቸው?

3. ከዚህ ሕክምና በተጨማሪ ሌሎች አማራጮች አሉ?

4. ይህን ሕክምና ባላደርግ ምን ይከሰታል?

የማህፀን በር ካንሰር ከኹሉም ካንሰር አይነቶች በኢንፌክሽን ተላላፊ የኾነውና ቀድም መከላከል ከሚቻሉ የካንሰር አይነቶች ዋነኛውና ሲኾን ስለዚህም ብናይ የመከላከል እርምጃዎቹ ስለተሳኩላቸው በምዕራባዊው ዓለም አሁን አሁን ላይ እጅጉን እየቀነሰ ይገኛል።

References

1. UpTodate 2018

2. Williams Gynecology 4th edition

3. FMOH, GUIDELINE FOR CERVICAL CANCER PREVENTION AND CONTROL IN ETHIOPIA, 2021