የቅድመ ቀዶ ህክምና ዝግጅቶች

በዶ/ር ኤደን በላይ (በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ሬዚደንት)

    ማንኛውም ታካሚ የቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው በሃኪሙ ከተነገረው በኃላ ከህክምናው አስቀድሞ አስፈላጊው ዝግጅት መደረግ አለበት:: ከቀዶ ህክምናዎ በፊት በሃኪምዎ የሚታዘዙ ምርመራዎችና አንዳንድ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንደ ኦፕሬሽኑ አይነትና ውስብስብነት ሊለያዩ ቢችሉም ከማንኛውም ቀዶ ህክምና በፊት መሰረታዊ የደም ምርመራዎች፣ የህመሙን ምንነትና ደረጃ ለመረዳት የሚያግዙ እንደ አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይና የናሙና ምርመራዎች ይከናወናሉ:: በተጨማሪም ታካሚው ስለሚሰራለት የቀዶ ህክምና ዓይነት፣ ህክምናው ባይደረግ ሊያጋጥመው ስለሚችል ጉዳት፣ በህክምናው ወቅት ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ችግሮች እንዲሁም አማራጭ ህክምና ስለመኖር አለመኖሩ ማብራሪያ ከተሰጠው በኃላ የስምምነት ቅፁን መፈረም ይኖርበታል::

 

ከማደንዘዣ ህክምና በፊት የሚደረግ መሰናዶ

የማደንዘዣ ህክምና በኦፕሬሽኑ ክብደትና ቅለት መሰረት የሚከናወን ሲሆን  በዋናነት 3 ዓይነት የማደንዘዣ ህክምናዎች አሉ:: እነዚህም፤

1. ህክምናው የሚደረግበትን የአካል ክፍል ብቻ አሊያም ያንን ክፍል የሚቆጣጠረውን ነርቭ በማደንዘዝና ህመም እንዳይሰማ በማድረግ የሚሰጥ ለቀላልና መለስተኛ ቀዶ ህክምናዎች           የሚያገለግል ( Local Anesthesia and Nerve blocks)

2. በህብለ-ሰረሰር በኩል የሚሰጥ ከእምብርት በታች ለሚከናወን ኦፕሬሽን የሚረዳ (Spinal Anesthesia)

3. እንዲሁም ታካሚውን ሙሉ በሙሉ በማስተኛት ከባድ የቀዶ ህክምና በሚከናወንበት ወቅት የህመም ስሜትም ሆነ ከህክምናው ጋር የተገናኘ ትውስታ እንዳይኖረው ለማድረግ የሚሰጥ የሰመመን ህክምና (General Anesthesia) ናቸው::

ተጓዳኝ ህመሞች

     ተጓዳኝ ህመም (የደም ግፊት ፣ የልብ ህመም ፣ የስኳር በሽታ ፣ የደም መርጋት ችግር ወ.ዘ.ተ) ላለባቸው ታካሚዎች ለሰመመን መድሃኒቶችም ሆነ ለቀዶ ህክምናው የጎንዮሽ ጉዳቶች ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ እና አስፈላጊውን ቅድመ-ጥንቃቄ ለማድረግ እንደየታካሚው የጤና ሁኔታ ተጨማሪ የደም ፣ የ ራጅ ፣ የልብና  ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ::  በተጨማሪም አጣዳፊ ያልሆኑ ቀዶ ህክምናዎች ተጓዳኝ ህመሞቹ በበቂ ሁናቴ እስከሚታከሙ ድረስ ቀዶ ህክምናው የሚከናወንበት ቀጠሮ ሊራዘም ይችላል:: 

መድሃኒቶች

   ታካሚው ለተለያዩ ተጓዳኝ ህመሞች የሚወስዳቸው መድሃኒቶች ካሉ ከሀኪሞች ጋር በሚደረግ ውይይት አንዳንዶቹን ለሰመመን ህክምናው አመቺ ወደሆኑ መድሃኒቶች በጊዜያዊነት መቀየር ፣ የሚወስዱትን መጠን ማስተካከል ብሎም ለተወሰነ ጊዜ ማቆም ሊያስፈልግ ይችላል::

ሲጋራና አልኮል መጠጥ

    በተጨማሪም ሲጋራና የአልኮል መጠጥ የሚጠቀሙ ታማሚዎች ከሰመመን ህክምና በኃላ ከፍተኛ የአተነፋፈስ መዛባትና የልብ ችግር ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ከቀዶ ህክምናው በፊት ቢያንስ ለአንድ ወር ከነዚህ አደንዛዥ ዕፆች ሊታቀቡ ይገባል::

ምግብና መጠጥ

       ማንኛውም ታካሚ ሙሉ ማደንዘዣ ከመውሰዱ በፊት በማደንዘዣ ወቅት በጨጓራ ውስጥ ያለ ምግብ ወደ አየር ቧንቧ እንዳይገባ ቢያንስ ለ8ሰዓታት ከቅባታማ ምግቦች፣ ለ 6 ሰዓታት ቀለል ካሉ ምግቦች፣ ለ2 ሰዓታት ከንፁህ ፈሳሾች (ውሃ፣ ለስላሳ፣ ቀጭን ሻይ…) መፆም ይኖርበታል:: ህፃናት ታካሚዎች ደግሞ ለ 4 ሰዓት የእናት ጡት ወተት ማቆም አለባቸው:: ነገር ግን የቀዶ ህክምናው አጣዳፊ በሚሆንበት ጊዜ ይህንን የጊዜ ገደብ መጠበቅ ላያስፈልግ ይችላል::

የደም ዝግጅት

    እንደ ቀዶ ህክምናው ዓይነት በህከምናው ወቅት መድማት ቢከሰት የሰውነትን ደም ለመተካት የሚያስችል  ከታካሚው የደም ዓይነት ጋር የሚጣጣም ደም በደም ባንክና ላቦራቶሪ በኩል እንዱዘጋጅ ይደረጋል።

በጥቅሉ ተገቢውን የቅድመ ቀዶ ህክምና ዝግጅት ማድረግ በህክምናው ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱ በተጨማሪ ቀዶ ህክምናው ውጤታማ እንዲሆን እና የመዳን ሂደቱም እንዲፋጠን ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

EMSA Digital Library

online platform where you can find resources

Fellowship Opportunities

International Opportunities For Young Leaders

ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ድንገተኛ እርዳታ ካስፈለግዎ

በነዚህ ቁጥሮች እርዳታ ያግኙ

Subscribe