የቤተሰብ እቅድ እና የወሊድ መከላከያ ምርጫዎች እና የተሳሳቱ አመለካከቶች

በረድኤት ወልደሩፋኤል (በቅድስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ህክምና ኮሌጅ ኢንተርን)

አርትኦት እና እርማት – በ ዶ/ር ምስክር አንበርብር (Gynecologist/Obstetrician)

የቤተሰብ እቅድ ምንድን ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚገልጸው የቤተሰብ እቅድ ግለሰቦችና ጥንዶች የሚፈለጉትን የልጆች ቁጥር እንዲሁም የሚወልዱበትን ጊዜ ለመወሰን የሚያስችል መንገድ ነው ።  ይህን ማድረግ የሚቻለው የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀምና መካንነትን በማከም ነው።

የወሊድ መከላከያ ምንድን ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የወሊድ መከላከያ ዘዴ ሰዎች የሚፈለጉትን የልጆች ቁጥር እንዲያገኙና እርግዝናቸው ባቀዱበት ጊዜ እንደሆን የሚያስችል የቤተሰብ እቅድ እንደሆነ ይገልጻል።

ወሊድ መከላከል በፈቃደኝነት የሚደረግ ሲሆን ውጤታማ እና በቀላሉ ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም እርግዝናን ለማዘግየት ወይም ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ይጠቅማል፡፡

የቤተሰብ እቅድ ማውጣትና የወሊድ መከላከያ  ምን ጥቅሞች አሏቸው?

  • ያልታሰበ እርግዝናን በመከላከል የእናቶችን የጤና መታወክ እና በእርግዝና ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር እንዲቀንስ ይረዳል።
  • ያልታሰበ እርግዝናን በመቀነስ የፅንስ ውርጃን ይቀንሳል።
  • ከአባላዘር በሽታዎች ይከላከላል።
  • የቤተሰብን የኢኮኖሚ እድገት ይጨምራል።

የቤተሰብ እቅድና የወሊድ መከላከያን በተመለከተ በጣም የተለመዱት የተሳሳቱ አመለካከቶች ምንድን ናቸው?

የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች በቤተሰብ እቅድና በስነ-ተዋልዶ ጤና ረገድ ወሳኝ ሚና ቢጫወቱም ከአጠቃቀም ጋር በተያያዘ አሁንም ድረስ ብዙ አፈ ተረቶችና የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ። እነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች የተሳሳተ መረጃን፣ ግራ መጋባትን እና እንዲያውም ግለሰቦች እና ጥንዶች የሚያስፈልጋቸውን የእርግዝና መከላከያ እንዳይጠቀሙ ይከለክላሉ፡፡ ከብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች እና አፈ ታሪኮች መካከል አንዳንዶቹ፤

  • በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ የወሊድ መከላከያ ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ያጋልጣል።
  • የወሊድ መከላከያ መሃንነት ያስከትላል።
  • የወሊድ መከላከያ የሴቶች ሃላፊነት ብቻ ነው።

 

በዚጽሑፍ ውስጥ ስለ የወሊድ መከላከያ አጠቃቀም በጣም የተለመዱ አፈ ታሪኮችን እና የተሳሳቱ አመለካከቶችን እናነሳቸዋለን፤ በተጨማሪም በተጨባጭ መረጃ እንሞግታቸዋለን።

የተሳሳተ አመለካከት #1፡ የወሊድ መከላከያ ወደ መሃንነት ሊመራ ይችላል።

ለረጅም ጊዜ የወሊድ መከላከያዎችን መጠቀም ወደ መሃንነት ሊያመራ ይችላል የሚል ሰፊ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። ነገር ግን ይህ እውነት እንዳልሆነ ጥናቶች አረጋግጠዋል። አብዛኛዎቹ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ከተቋረጡ በኋላ የመውለድን ሁኔታ አይጎዱም። ለምሳሌ፡ የወሊድ መከላከያ ክኒኖችን ሲጠቀሙ የቆዩ ሴቶች መድሃኒቱን ካቆሙ በኋላ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ የመውለድ ችሎታቸው ተመልሶ እንደሚመጣ ሊጠብቁ ይችላሉ፡፡ በመርፌ የሚሰጥ የእርግዝና መከላከያ (ዴፖ) የሚጠቀሙ ሴቶች መርፌውን መጠቀም ከቆሙ በኃላ ወደ ቀድሞ የልጅ መውለድ አቅም ለመመለስ ከ6ወር እስከ 1 አመት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ይህ ግን ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን(እንደ የወንዶች የዘር መተላለፊያ ቱቦ መዝጋት ወይም ቫሴክቶሚ) የማያካትት መሆኑን ያስተውሉ።

የተሳሳተ አመለካከት #2፡ የወሊድ መከላከያ የሰውነት ክብደት እንዲጨምር ያደርጋል

ስለ የወሊድ መከላከያ ሌላ የተለመደ አፈ ታሪክ ክብደት እንዲጨምር ያደርጋሉ የሚለው ነው፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች አዲስ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ሲጀምሩ ትንሽ የክብደት መለዋወጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ይህም የእርግዝና መከላከያው ራሱ የሚያመጣው ሳይሆን ፕሮጄስትሮንን የሚይዙ የእርግዝና መከላከያዎች የምግብ ፍላጎት ስለሚጨምሩ የክብደት መጨመር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

የእርግዝና መከላከያዎችን በሚጠቀሙበት ጊዜ ስለ ክብደት መጨመር ስጋት ካለብዎ ከጤና ባለሙያ ጋር መማከር አስፈላጊ ነው።

የተሳሳተ አመለካከት #3፡ የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ፅንስ ማስወረድ ያስከትላል።

የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ(morning-after pill)  ወይም ፕላን B በመባል የሚታወቀው የእርግዝና መከላከያ ፅንስ ያስወርዳል የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ የድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ጥንቃቄ ካልተደረገበት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም እንደ ኮንዶም መቀደድ አጋጣሚ በኋላ  ጥቅም ላይ ሚውል ሲሆን፣ እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት ያሉትን የኦቭዩሌሽን(ovulation) እና የፈርትላይዜሰሽን (fertilization) ሂደቶች እንዳይፈጠሩ ይደረጋል። ነባሩን እርግዝና አያቋርጥም ወይም በማደግ ላይ ያለ ፅንስ ካለ አይጎዳም።

የተሳሳተ አመለካከት # 5: የማህፀን ውስጥ መሳሪያ ወደ ማህፀን ውስጥ ዘልቆ በመግባት ወደ ልብ ሊሄድ ይችላል

IUD ወይም በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ  የወሊድ መከላከያ፣ እርግዝናን ለመከላከል በማህፀን ውስጥ የሚገቡ ትናንሽ T-ቅርጽ ያላቸው መሳሪያዎች ናቸው። የማህፀን ውስጥ የሚቀመጡ የወሊድ መከላከያ በማህፀን ውስጥ እንዲቆይ እና ወደ ሌሎች ራቅ ያሉ የሰውነት ክፍሎች እንደ ልብ እንደማይሰደዱ ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው። አሰራራቸው በማህፀን ውስጥ እንዲቀመጡ እንጂ በመላ ሰውነት ውስጥ በነፃነት መንቀሳቀስ አያስችላችውም።

በተጨማሪም ማህፀን የማህፀን ውስጥ የሚቀበር የወሊድ መከላከን በጠበቀ ሁኔታ የሚይዝ ጡንቻማ አካል ነው።  የማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ የወሊድ መከላከያ ከማህፀን ውስጥ ዘልቆ የማለፍ አጋጣሚዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ወደ ልብ እና ራቅ ወዳለ ሌላ   የሰውነት አካል ውስጥ አይሰደዱም።

 

የተሳሳተ አመለካከት #6፡ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች በሕፃናት ላይ የአፈጣጠር ችግርን ያስከትላሉ።

 

አንዳንዶች አንዲት ሴት የወሊድ መከላከያ እየተጠቀመች ካረገዘች የወሊድ መከላከያ መጠቀሙ ህፃኑን እንደሚጎዳ ያምናሉ፣ ነገር ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በአጠቃላይ ዘመናዊ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒኖች፣ ማህፀን ውስጥ የሚገቡ መሳሪያዎች (IUDs)፣ በክንድ የሚቀበሩ የወሊድ መከላከያዎች እና መርፌዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ ተደርገው ይወሰዳሉ እናም በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ እርግዝናን ይከላከላሉ፣ በአጠቃቀም ስህተት ወይም በሌላ ምክያንት እርግዝና ቢፈጠር ግን በጽንሱ ላይ የአፈጣጠር ችግር የመጋለጥ እድልን አይጨምሩም።

የተሳሳተ አመለካከት #7፡ የወሊድ መከላከያ ለሴቶች ብቻ ነው።

ስለ የወሊድ መከላከያ በጣም ከተለመዱት የተሳሳቱ አመለካከቶች አንዱ ለሴቶች ብቻ ነው የሚለው አመለካከት ነው፡፡ ለሴቶች ብዙ የወሊድ መከላከያ አማራጮች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ለወንዶችም በርካታ አማራጮች አሉ። የወንድ ኮንዶም እና የወንዶች የዘር መተላለፊያ ቱቦ መዝጋት (ቫሴክቶሚ) ሁሉም ውጤታማ የወንድ የወሊድ መከላከያ ዓይነቶች ናቸው።

ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ሁለቱም አጋሮች የወሊድ መከላከያ ሃላፊነትን መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡

 

References

Family planning, A global handbook for providers 2018 ED, WHO

WHO fact sheet, November 2020

https://www.who.int/health-topics/contraception

https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/family-planning-contraception

https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC8739061/

https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC7661170/