የትራማዶል ሱስና መዘዙ

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ “ትራማዶል” በተባለ መድኃኒት አጠቃቀም እና ስርጭት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሆነ አስታውቋል። ለመሆኑ ይህ መድኃኒት ምንድነው? ከሌሎች መድኃኒቶች በተለየ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት የሆነውስ በምን ምክንያት ነው? ማህበረሰባችንስ ስለ መድኃኒቱ ምን ማወቅ ይኖርበታል?

 

ትራማዶል ምንድነው?

ትራማዶል በሰው ልጅ መደበኛ አእምሮአዊ ሁኔታ ላይ ጫና የሚያሳድር (ሳይኮትሮፒክ የሆነ) እንዲሁም ተለምዶአዊ ስሜትና ጠባይ ላይ ለውጥ የሚያመጣ (ናርኮቲክ) የመድኃኒት ዓይነት ነው። መድኃኒቱ በዋናነት ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ለሆነ ህመም በተለይም ከቀዶ ህክምና በኋላ እና በወሊድ ምክንያት ለሚኖር ህመም እንደ ማስታገሻነት ያገለግላል። ከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ ወይም ሌሎች ዓይነት የነርቭ ጉዳቶች የሚያመጡትን ህመም ለማስታገስም ለታካሚዎች ይሰጣል። በተጨማሪም ከሌሎች የህመም ማስታገሻዎች ጋር አንድ ላይ በመሆን የጉልበትና ጭን ህመሞችን ለማስታገስና ከህመም ስሜቱ ፋታን ለማስገኘት ያስችል ዘንድ ታካሚዎች እንዲወስዱት ይደረጋል።

የትራማዶል ትክክለኛ አወሳሰድ ምን ይመስላል?

ትራማዶል በክኒን የሚወሰድ ወይም ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ በፈሳሽ መልክ ተዘጋጅቶ በደምስር የሚሰጥ ሲሆን መጠን እና የአሰጣጥ መንገዱ በታካሚው እድሜ፣ ክብደት፣ ሌሎች የጤና እክሎች፣ ሌሎች በመወሰድ ላይ ባሉ መድኃኒቶችና በመሳሰሉ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ በህክምና ባለሞያዎች ውሳኔና ቁጥጥር እየተደረገበት ለታካሚው ይሰጣል። ይህን መድኃኒት ከ50-100 ሚሊግራም በሆነ መጠን በቀን ከ4 ጊዜ በላይ መውሰድ በህክምና ባለሞያዎች አይመከርም። ምክንያቱም መድኃኒቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጓዳኝ ለረጅም ጊዜ ከተወሰደ ወይም ደግሞ ከታዘዘው መጠን በላይ ከተወሰደ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላሉት ነው።

 

ትራማዶል የሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች ምን ምን ናቸው?

  • የአእምሮ ስራ መቀነስና መፍዘዝ
  • ማቅለሽለሽ
  • ማስመለስ
  • የአፍ መድረቅ
  • የራስ ምታት
  • የሆድ ድርቀት
  • የእንቅልፍ ማጣት
  • እንዲሁም የሚጥል በሽታ ላለባቸው ታካሚዎች ከተሰጠ ህመማቸውን ይቀሰቅሳል፤ ያባብሳል።

 

በትራማዶል ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉ ለምን አስፈለገ?

ትክክለኛ እና ተገቢ በሆነ መንገድ ሲወሰድ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ትራማዶል፣ ያለህክምና ባለሞያ ትእዛዝ ሲወሰድ በአእምሮአዊና አካላዊ ጤና ላይ አደገኛ ጉዳትን ያመጣል።  የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣንም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ዓመታት ባደረጋቸው ጥናቶች ትራማዶልን አብዛኛው የማህበረሰባችን ክፍል በተለይም በአፍላ ወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ያለሐኪም ትእዛዝና ያለበቂ ምክንያት እንደሚጠቀሙት ሊታወቅ ችሏል።

Photo from – https://www.globenewswire.com/news-release/2017/12/04/1219734/0/en/Drug-News-Outlet-TheRecover-com-Sheds-Light-On-College-Substance-Abuse.html

 

ትራማዶል በዋነኝነት በማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓታችን ላይ ስለሚሰራ በአንጎላችን ላይ ጫናን በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የህመም መታገስን፣ ፋታ የማግኘትን እና የደስታን ስሜት ይሰጣል። በዚህም ምክንያት መድኃኒቱ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለረጅም ጊዜ ከተወሰደ ሱስ የማስያዝ እና ተጠቃሚው በመድኃኒቱ ላይ ጥገኛ እንዲሆን የማድረግ አቅም አለው። ስለሆነም ይህንን መድኃኒት ተገን አድርጎ መንቀሳቀስ የለመደ ወጣት፣ ከፍተኛ የሱስና የጥገኝነት ስሜት ውስጥ ስለሚገባ መድኃኒቱን መጠቀም በማይችልባቸው ሁኔታዎች ላይ በገዛ አካሉና አእምሮው ላይ መስራትና ማዘዝ የማይችል ደካማ ወጣት ይሆናል ማለት ነው።

 

በተጨማሪም በትራማዶል ሱስ የተዘፈቁ ወጣቶች የሚከተሉት እክሎች ይገጥሟቸዋል።

  • ጤናማ ያልሆነ የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ
  • ለረጅም ሰዓታት መተኛት
  • የመደበትና የመጨነቅ ስሜት
  • የአእምሮ ንቃትና ትኩረት በእጅጉ መቀነስ
  • ጤናማ ያልሆነ የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ
  • ዝቅተኛ የትምህርት ወይም የስራ አፈጻጸም ማስመዝገብ
  • ጤናማ ያልሆነ የጠባይ ለውጥ
  • የፍላጎትና የተነሳሽነት ማጣት . . . ወ.ዘ.ተ. ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህም በላይ ወጣቶች መድኃኒቱን በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠቀሙበት ወቅት ገበያ ላይ ያለው ተደራሽነት በእጅጉ ስለሚመናመንና ዋጋውም በጣም ስለሚጨምር፣ መድኃኒቱ በህክምና ታዞላቸው በአፋጣኝ ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ከባድ ፈተናን ይጋርጣል።

 

ይህንን ችግር ለመቅረፍ እነማን ምን ያድርጉ?

ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል ያስችል ዘንድ በትራማዶል ግዢ፣ ሽያጭና አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚደረግ እንዲሁም መድኃኒቱ ከዚህ በፊት ሲታዘዝበት ከነበረው በተለየና በህክምና  ባለሞያዎች እጅ ብቻ በሚገኝ የማዘዣ ወረቀት እንዲታዘዝ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በዚህ የቁጥጥር ስራ ላይም መንግስት ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሞያዎች፣ በመድኃኒት ምርትና ሽያጭ ላይ የተሰማሩ አካላትና መላው ማኅበረሰባችን በተለይም ወጣቶች የበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባናል። ከሚሰራው የቁጥጥር ስራ በላቀ ሁኔታ ግን ማኅበረሰባችን በመድኃኒቱ ዙርያ ያለውን ግንዛቤ ከጊዜ ወደጊዜ እንዲያሳድግ በመስራት የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ አፍላ ወጣቶችን ህይወት ከመሰናከል ልናተርፍ ይገባናል።

 

በጤና ያቆየን!

ዮርዳኖስ ታዬ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, PC-1

 

 

ዋቢ

  • ጤና ሚኒስቴርኢትዮጵያ – Dawit. (2022, Nov. 01). “Tramadol is listed and under strict control of narcotic drugs – Ethiopian Food and Drug Authority”. Ministry of Health – Ethiopia. https://www.moh.gov.et/site/node/414
  • Fana Broadcasting Corporate – Abate, Kidist. (2022, November 01). “Authority Restricts OTC Tramadol Usage”. Fana Broadcasting Corporate. https://www.fanabc.com/english/authority-restricts-otc-tramadol-usage/
  • Katzung B.G., & Kruidering-Hall M, & Trevor A.J.(Eds.), (2019). Katzung & Trevor’s Pharmacology: Examination & Board Review, 12e. McGraw Hill.
  • Brunton L.L., & Hilal-Dandan R, & Knollmann B.C.(Eds.), (2017). Goodman & Gilman’s: The Pharmacological Basis of Therapeutics, 13e. McGraw Hill.
  • DiPiro J.T., & Yee G.C., & Posey L, & Haines S.T., & Nolin T.D., & Ellingrod V(Eds.), (2020). Pharmacotherapy: A Pathophysiologic Approach, 11e. McGraw Hill.
  • Rang, H.P., Dale, M.M. and Ritter, J.M. (2020) Rang and Dale’s Pharmacology. Edinburgh etc.: Elsevier.
  • Kaliszewski, Michael. (2022, September 12). “Painkiller Abuse Among College Students”. American Addiction Centers. https://americanaddictioncenters.org/rehab-guide/college/painkiller-abuse