የአባላዘር በሽታዎች (SEXUALLY TRANSMITTED INFECTIONS)

የአባላዘር በሽታዎች (SEXUALLY TRANSMITTED INFECTIONS)

በ- ማህሌት አላምነው ሀይሌ (ሚዮንግሳንግ የህክምና ኮሌጅ -1ኛ አመት (PC1)

አርትኦት እና እርማት – በ ዶ/ር ምስክር አንበርብር (Gynecologist/Obstetrician)

 

የአባላዘር በሽታዎች ምንድን ናቸው?

የአባላዘር በሽታ (SEXUALLY TRANSMITTED INFECTIONS) በዋናነት በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው። የአባላዘር በሽታ ከሰው ወደ ሰው በደም፣ በግንኙነት ጊዜ በሚፈጠሩ ፈሳሾች፣ እንዲሁም ከእናት ወደ ልጅ በእርግዝና ጊዜ ወይም በውልደት ጊዜም ሊተላለፉ ይችላል።

እንደ አለም ጤና ድርጅት ሪፖርት 30 በላይ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ እና ጥገኛ ተውሳኮች ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች መከሰት ምክንያት ናቸው። የአባላዘር በሽታዎች በአብዛኛው ጊዜ ምልክት አያሳዩም። በዚህም ምክንያት ጤነኛ ተብሎ የሚታሰብ ሰው በቀላሉ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል።

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?

የአባላዘር በሽታዎች በየፊናቸው የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳዩም ወይም ላያሳዩም ይችላሉ።

ሊታዩ ከሚችሉ ምልክቶች ወስጥ ከታች የተዘረዘሩት ተጠቃሽ ናቸው፦

  • በብልት እና አካባቢው እብጠት፣ቁስለት እና የህመም ስሜት
  • ሽንት በሚሸናበት ጊዜ ሕመም ወይም የማቃጠል ስሜት
  • ከብልት ያልተለመደ ሽታ እና መልክ ያለው ፈሳሽ ማየት
  • የብልት መድማት
  • በግንኙነት ጊዜ ያልተለመደ የሕመም ስሜት እና
  • ትኩሳት፣ የመሳሰሉት ምልክቶች ተጠቃሽ ናቸው።

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ለበሽታው ከተጋለጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሊታዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለአመታት ከባድ የሚባል ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል።

የተለያዩ አይነት የአባላዘር በሽታዎች አሉ። ከነዚህም መካከል ጥቂቶቹ  የሚከተሉት ናቸው፦

ጨብጥ (GONORRHEA)

በባክቴሪያ የሚመጣ የአባላዘር በሽታ ነው። ጨብጥ የያዘው ግለሰብ በሽንት ጊዜ የማቃጠል ስሜት ሊያሳይ ይችላል። በተጨማሪም ከብልት ውስጥ ነጭ፣ ቢጫ ወይም አረንጓዴ ፈሻሽ ሊወጣ ይችላል። በአብዛኛው ጊዜ ጨብጥ በሴቶች ላይ ምልክት አያሳይም።

ቂጥኝ (SYPHILIS)

ቂጥኝ በባክቴሪያ የሚመጣ የአባላዘር በሽታ ነው። በጊዜ ካልታከመ ከባድ የሆነ የጤና ችግሮችን ያስከትላል። ቂጥኝ የሚተላለፈው  በግንኙነት ጊዜ በሚከሰት ንክኪ ነው።

ቂጥኝ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፦

አንደኛ ደረጃ (PRIMARY SYPHILIS)

የቂጥኝ የመጀመሪያ ምልክት በብልት አካባቢ ቁስለት ሲሆን ለበሽታው ከተጋለጡ 3 ሣምንት በኋላ ሊታይ ይችላል። ቁስለቱ የህመም ስሜት የለውም እና በሴቶች ላይ የመደበቅ ባህርይ አለው። 3-6 ሳምንት በኋላ ቁስለቱ በራሱ ይድናል።

ሁለተኛ ደረጃ (SECONDARY SYPHILIS)

ቁስለቱ ከዳነ ከጥቂት ሳምንት በኋላ በመሉ ሰውነት ላይ የሽፍታ ምልክት ይታያል። በእጅ እና በእግር መዳፍ ላይ ሽፍታ ይስተዋላል።  ሽፍታው የማሳከክ ስሜት የለውም እና በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች የፀጉር መርገፍ፣ የጡንቻ ህመም፣ ትኩሳት እና የጉሮሮ ህመም ያጋጥማቸዋል። እነዚህ ምልክቶች እየመጡና እየጠፉ ለዐመታት ሊቆዩ ይችላሉ።

ሶሰተኛውና ደረጃ (TERITARY SYPHILIS)

በጊዜ ህክምና ያላገኙ ታካሚዎች ሌሎች ተጓዳኝ የጤና እክሎች ያጋጥማቸዋል። ከነዚህም መካከል በአንጎል፣ በነርቮች፣ በዓይን፣ በልብ፣ በደም ሥሮች፣ በጉበት፣ በአጥንትና በመገጣጠሚያ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ክላሚዲያ (CHLAMYDIA)

ክላሚዲያ በባክቴሪያ የሚተላለፍ የአባላዘር በሽታ ሲሆን በቀላሉ የመዳን እድል አለው። እንደ ጨብጥ በሴቶች ላይ ምልክት አያሳይም። የክላሚዲያ ዋነኛ ምልክት በግንኙነት ጊዜ ያልተለመደ የሕመም ስሜት እና ከብልት ያልተለመደ ፈሳሽ ማየት ናቸው።  ክላሚዲያ በጊዜ ካልታከመ በሴቶች እና በወንዶች ላይ መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል።

የአባላዘር በሽታዎች እና ተያያዥ ጉዳቶች

የአባላዘር በሽዎች ወዲያውኑ ከሚያስከትሉት ጉዳቶች የበለጠ ከባድ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ለምሳሌ፦

  •   የአባላዘር በሽታ ከእናት ወደ ልጅ ሲተላለፍ የፅንስ መጨንገፍ፣ የተወለዱ ህፃናት የክብደት መቀነስ፣ ወይም የህፃናት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ሊያስከትል ይችላል።
  •   በተጨማሪም የኤችአይቪ ኤድስ ተጋላጭነትንም ይጨምራል

የአባላዘር በሽታዎች የመከላከያ መንገዶች

የአባላዘር በሽታዎችን በቀላሉ መከላከል ይቻላል። በተለይም የፆታ ግንኙነት የጀመረ ግለሰብ እራሱን እና አጋሩን እንዴት መጠበቅ እንደሚችል ማወቅ አለበት።

የአባላዘር በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት በቀዳሚነት በፆታዊ ግንኙነት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።

  •     በግንኙነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም
  •     የወሲብ አጋር አለማብዛት
  •     መታቀብ
  •     ምርመራዎችን እና ህክምናዎችን ማድረግ
  • በበሽታው የተያዘ ሰው በበሽታው ደግሞ ላለመያዝ እና  የአጋሩን ጤና ለመጠበቅ ለአጋሩ በሽታው እንዳለበት/እንዳለባት  በመግለፅ  አጋሩ ምልክት ባይኖራትም/ባይኖረውም ህክምና አንድታገኝ/እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ነው።
  • የአባላዘር በሽታዎች ስርጭትን ለመቀነስ በቤት ውሰጥ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ከታዳጊ ልጆች ጋር ስለዚህ ጉዳይ በግልፅ ውይይት ማድረግ፣ በትምህርት ቤቶች የስነፆታ ትምህርት ማስፋፋትና ማጠናከር፣ የስነፆታ ጤና መረጃና ትምህርትን በተለይም በአባላዘር በሽታዎች የመተላለፊያ መንገዶች እና የመከላከያ መንገዶችን መረጃ ማቅረብ ይመከራል፡፡

የአባላዘር በሽታዎች ምርመራ

የአባላዘር በሽታዎች በአብዛኛው ጊዜ ምልክቶች አያሳዩም። ስለዚህ አብዛኛው በላብራቶሪ ምርመራ ላይ የተመሰረተ ነው። የደም የሽንት እና የፈሳሽ ምርመራ በሽታው መኖሩን እና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ይጠቅማሉ።

ምርመራዎች የበሽታው መኖርና አለመኖሩን ከማረጋገጥ ባለፈም፦

  •   ምልክት የሚያሳዩትን ከማያሳዩት ለመለየት
  •   የፆታዊ ግንኙነት አጋር ተጋላጭነትን ለማረጋገጥ
  •   በእርግዝና ወቅት የፅንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ
  •   ከተወለደም በኋላም የህፃኑን ጤንነት ለማረጋገጥ መጠቀም ይቻላል።

 

የአባላዘር በሽታዎች ሕክምና

  • አባላዘር በሽታ ህክምና በሚታዩት ምልክቶች ላይ ይወሰናል። እናም ህክምናውን ለመጀመር አብዛኛውን ጊዜ የላብራቶሪ ምርመራ አያስፈልግም። ሆኖም ግን አንዳንድ ግዜ እነዚህ ምርመራዎች አስፈላጊ ሆነው ከተገኙ በጤና ባለሙያዎች ታዘው ሊሰሩ ይችላሉ።
  • በአሁኑ ጊዜ ለበርካታ የአባላዘር በሽታዎች ዓይነት ውጤታማ የሆነ ሕክምና ማግኘት ይቻላል ክላሚዲያ፣ ቂጥኝ ጨብጥ እና አንድ ጥገኛ ተውሳክ የአባላዘር በሽታ አምጪ (ትሪኮሞኒያሲስ) በነጠላ በሚወስዱ መድሃኒቶች አማካኝነት በአብዛኛው ሊፈወሱ የሚችሉ ናቸው።

 

  • ለኸርፐስና (HERPES) ለኤች አይ (HIV) በጣም ውጤታማ የሆኑት መድኃኒቶች በሽታውን ሊፈውሱ ባይችሉም የበሽታውን አካሄድ ሊቀንሱ የሚችሉ ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች አሉ።

 

በሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ የአባላዘር በሽታዎች 9.4% እስከ 21% የሚሆን የስርጭት ስፋት አላቸው። ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛውን ስፍራ የሚይዙት 15-24 እድሜ ክልል ወስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በወጣቶች ዘንድ የአባላዘር በሽታ  ስርጭት እየጨመረ መጥቷል። በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተካሄደ ጥናት የአባላዘር በሽታ ስርጭት 18.20% መሆኑን አረጋግጧል። ከበርካታ ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት መፈፀም፣ በጾታ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም አመጠቀም፣ እንዲሁም ወጣቶች ስለ አባላዘር በሽታ  ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ለበሽታዉ መስፋፋት አስተዋፅኦ አድርጓል።

 

SOURCES

  •       World Health Organization. (n.d.). Sexually transmitted infections (stis). World Health Organization. https://www.who.int/health-topics/sexually-transmitted-infections#tab=tab_3
  •       Mayo Foundation for Medical Education and Research. (2023, September 8). Sexually transmitted diseases (stds). Mayo Clinic. https://www.mayoclinic.org/diseases-conditions/sexually-transmitted-diseases-stds/symptoms-causes/syc-20351240
  •       Elizabeth Boskey, P. (n.d.). The most common sexually transmitted infections (stis). Verywell Health. https://www.verywellhealth.com/the-most-common-stds-sexually-transmitted-diseases-3133040
  •       Kassie, B. A., Yenus, H., Berhe, R., & Kassahun, E. A. (2019, November 8). Prevalence of sexually transmitted infections and associated factors among the University of Gondar students, Northwest Ethiopia: A cross-sectional study – reproductive health. BioMed Central. https://reproductive-health-journal.biomedcentral.com/articles/10.1186/s12978-019-0815-5

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg