የአእምሮ ጤና እና የህክምና ተማሪዎች

(ሚክያስ ማዕረጌ – ጎንደር ዩንቨርሲቲ አራተኛ አመት የህክምና ተማሪ) 

የአለም የጤና ድርጅት በ2019 ባደረገው ጥናት ወደ አንድ ቢልየን የሚጠጋ ሰው   ጤና መጓደል እንደሚሰቃይ ተናግሯል። በቀጣዩም አመት ማለትም በፈረንጆቹ 2020 ይህ ቁጥር በ25% ከፍ እንዳለ በጥናቱ ላይ አካትቷል። ይህ ማለት በደምሳሳው ከስምንት ሰዎች አንዱን ከአእምሮ ጤና  መጓደል በሽታዎች ውስጥ አንዱ ያጠቃዋል ማለት ነው።[1]ብዙ የጥናት ጽሁፎች በአለም ላይ ከሌሎች በሽታዎች የበለጠ ብዙ ሰውን የሚያጠቃው የአይምሮ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ። [2] ከዚህ ጽሁፍ አንባቢዎችም ውስጥ ብዙዎቹ በዚህ በሽታ የተጠቁ የመሆናቸው እድሉም ከፍተኛ ነው። እንደዚህ ብዙ ሰዎችን የሚያጠቃ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ብዙ ስለ አእምሮ ጤና መጓደል የማንሰማው ለምንድን ነው? ለመሆኑስ የአእምሮ ጤና መጓደል ምንድን ነው?

 

እንደ አለም ጤና ድርጅት ገለጻ የአእምሮ ጤና መጓደል ወይም Mental Disorder ማለት “አንድ ሰው ባለው ጤናማ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባህርይ ላይ የሚፈጠር መታወክ፣ ከዚህም የተነሳ ድሮ የሚሰራቸውን ተግባራት መስራት ሲያቅተውና በሽታው የእለት ተእለት ኑሮውን እንዳይኖር እንቅፋት ሲሆንበት ነው።”[3] ብሎ ይገልጸዋል።

 

ርዕሱ የሚፈራና ብዙ ጊዜ የሚደፈር መወያያ ባይሆንም ስለ አእምሮ ጤና ብዙዎቻችን ሰምተናል፣ አይተናል የምናውቀውም ሰው ይኖራል። ነገር ግን በሃገራችን የአእምሮ ችግር ተብሎ የሚነገረው እና ህዝቡም የሚያውቀው ከአእምሮ ጤና ችግሮች ውስጥ በጣም ውስን የሆነና ትንሽ ክፍል ነው። ማንም ሰው የአእምሮ ጤና ችግር ሲባል ቀድሞ ወደ ሃሳቡ የሚመጣው በሰንሰለት ታስረው ወደ ጸበል የሚወሰዱ፣ መንገድ ላይ እርቃናቸውን የሚሄዱ፣ በአእምሮ ሆስፒታሎች ውስጥ ኑሯቸውን ያደረጉ፣ ድንጋይ የሚወራወሩ፣ በህብረተሰቡ የተገለሉና፣ ከህብረተሰቡ ጋር ለመኖር የማይሆኑ ህሙማንን ነው። የብዙዎቻችን አስተዳደግና ህብረተሰቡ ይሄንን ነው እንድናስብና እንድናይ የሚያደርገን። ከዚም ጋር አብሮ የሚመጡ ብዙ ማግለሎችና ማሸማቀቆች አሉ። ይሄ ግን ከአእምሮ በሽታ ብዙ መልኮች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። የአእምሮ ጤና መታወክ በጣም ሰፊ የሆነ የበሽታ ክፍል ሲሆን በየቀኑ ሊያጋጥመን ከሚችለው በተለምዶ ድብርት ከምንለው     ሁሉ ያጠቃልላል። ስለ እያንዳንዱ ማብራራት ከጀመርን ጽሁፉ የማያልቅ ስለሚሆን በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በደንብ ለማውራት ስላሰብኩት በተለይ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ማእከላት ባሉ ተማሪዎች ላይ የተለመዱ የሆኑትን አንስተን እንወያያለን።

 

ተማሪዎች ወደ ዩንቨርሲቲ በሚቀላቀሉበት ጊዜ ከአካዳሚክ ሸክሙ በተጨማሪ ከቤተሰብ መለየትና ወደማያውቁት አዲስ ቦታ መሄዳቸውም ጭምር በላያቸው ላይ የሚጫነውን ሃላፊነት ያከብደዋል። ስለ ህክምና ትምህርት ካነሳን ደግሞ እነዚህ ነገሮች በእጥፍ ይጨምራሉ። ያለው የንባብ ብዛት፣ ትምህርቱ የሚጠይቀው ጊዜ፣ የእንቅልፍ መዛባትና የእንቅልፍ እጦት፣ የውጤት መበላሸትና ከአስተማሪዎች ጋር የሚኖር መስተጋብር የተማሪዎችን የአእምሮ ጤና የሚያውኩ ገፊ ሃይሎች ናቸው።

 

ድባቴ (Depression) ስሜታችን ፍላጎታችንና ድርጊቶቻችን ላይ በአሉታዊ መልኩ ተጽእኖ ያሳድራል። በዋናነት ታማሚው የሃዘን ስሜት ውስጥ ረዥም ጊዜ ያሳልፋል፣ ድሮ በደስታ የሚያደርጓቸው ድርጊቶች አሁን ስሜት አይሰጧቸውም። እንደ ድባቴው ክብደትና ቅልለት የተለያዩ ምልክቶች ይኖረዋል። ለምሳሌ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የእንቅልፍ መርሃ ግብር መዛባት፣ ለራስ ዋጋ ማጣት፣ በራስ መተማመን መቀነስ የመሳሰሉት ናቸው።[4]

 

ብዙ ተማሪዎች በዚህ ጉዳይ የሚሰቃዩ ቢሆንም ነገሩ የአእምሮ ጤና ችግር እንደሆነ የሚረዱና ህክምናን የሚሹ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ በጣም ትንሽ ነው። ብዙ ተማሪዎች በህክምና ትምህርት ውስጥ በማለፋቸው የሚገጥሟቸው ነገሮች የህክምና እርዳታ የሚፈልጉ እንደሆነ አያስቡም። ከህክምና ትምህርቱ በሚላቀቁ ጊዜ የሚተዉአቸው ቀላል ነገሮች እንደሆኑ ነው የሚያስቡት። ትክክለኛ ያልሆነ ፍርሃት፣ ማጥናት አለመቻል፣ በአስተማሪ ፊት ጥያቄን መጠየቅም መመለስም መፍራት፣ በራስ መተማመንን ማጣት፣ ለራስ ያለ ዋጋ መቀነስ እንዲሁም ሌሎች የመሳሰሉ ምልክቶችን ከአእምሮ ጤና መታወክ ጋር አያይዞ ከማየት ይልቅ እነዚህን ባህሪዎች የህክምና ትምህርት ከመማር ጋር የሚመጡ አይቀሬ ልምዶች፣ ከነሱም በፊት የነበሩ ተማሪዎች የነበሩባቸው፣ ከነሱም ኋላ የሚመጡ ተማሪዎች የሚደርሱባቸው እንደሆኑ ማሰብ ይቀልላቸዋል። እነዚህንም ነገሮች ለመቋቋም የህክምና እርዳታ ከመሻት ይልቅ ተማሪዎች ሱስ ውስጥ ራሳቸውን ሲከትቱ ማየት የተለመደ ሆኗል። ብዙ ተማሪዎች ራሳቸውን ከባድ ጭንቀት ወይም Anxiety ውስጥ እንደሆኑ አያስቡም። በCovid 19 እና እሱን ተከትሎ ለነበረው ረዥም እረፍት ምክንያትም Clinical Depression ወይም ድባቴ ከተለምዶ “ድብርት” ከምንለው ስሜት ጋር የሚለየው መስመር እጅግ ፈዛዛ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ ተማሪዎች ድባቴ ውስጥ ሆነው ይሆን ወይም የትምህርቱ ሸክም ከብዷቸው ማወቅ ከባድ ይሆንባቸዋል።

 

ህመማቸው የሚያውቁም ሆነው ለሌሎች ተማሪዎችም ለመናገር ፈቃደኛ የሚሆኑ ትንሽ ናቸው። ቢናገሩም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ የሚሆን አይነት እርዳታ አያገኙም። በድባቴ እየተሰቃየ ያለ ተማሪ ለእኩዮቹ ቢያወያይ፣ “ፈታ በል” የሚል የትም የማያስኬድ ‘ምክር’ ሊያገኝ ይችላል።

 

ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ከአእምሮ ህመም ጋር ተያይዞ ያለው መገለልና ማሸማቀቅ ተማሪዎች የባለሞያ እርዳታን እንዳይፈልጉ በማድረግ ዋናውን ቦታ ይይዛል። ለምሳሌ በምንማርበት ሆስፒታል ውስጥ የስነ አእምሮ ዲፓርትመንትና የህክምና ክፍል (Psychiatry Department and Ward)   እንደ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ለተማሪው በነጻ ካርድ አውጥቶ መታከም የሚቻልበት ሁኔታም አለ። በዘርፉም ጥሩ እውቀት ያላቸው ባለሞያዎችም አሉ። ነገር ግን እኔንም ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ይሄንን አገልግሎት የሚጠቀም ብዙ ሰው የለም።

 

ለምን? እንደው እንኳ ራሴን እንደምንም አሳምኜ ካርድ አውጥቼ ለመታከም ባስብ ራሱ፣ ወደ ሳይካያትሪ ዋርድ ስሄድ የሚያዩኝ ተማሪዎች የሚጠይቁኝ ጥያቄ ያሸማቅቀኛል። መንገድ ላይ ማንም ሳያየኝ ወደ ዋርድ ሄድኩኝ ብል ራሱ፣ የመማሪያ ሆስፒታል እንደመሆኑ በሳይካያትሪ ዋርድ ውስጥ Attach እያደረጉ ያሉ፣ Internship ላይ የሚገኙና ትምህርት የሚማሩ (ብዙዎቹን በርቀትም በቅርብም የማውቃቸው) ተማሪዎች ያዩኛል።  እነዚህ ልጆች ሲያዩኝ የሚያስቡትን እፈራለሁ። ለጓደኞቻቸው ተናግረው “የእብዶች ዋርድ” አየነው ተብሎ ሰው ሲጠቋቆም ያሸማቅቃል። ስለዚህ አለመሄድን እመርጣለሁ። ካገኘሁት ሰው ምክርን መጠየቅ ይቀልለኛል። ይህ ደግሞ ላልሆነ ምርመራ (Diagnosis) እና መድሃኒት መውሰድ ያጋልጣል።

 

በሃገራችን በተለይ የአእምሮ ጤና ጉዳይ በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፣ ተከታታይና በቂ ጥናትም አልተደረገበትም ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ ቁጥሮችን አንስቶ ከተማሪዎች ውስጥ በፐርሰንት ምን ያህል እንደተጠቃ ለመናገርም ከባድ ነው። ይህ ግን መቀረፍ ያለበት ችግር ነው።

Mental Health Status of 150 Medical Students (https://www.nejm.org/doi/full/10.1056/NEJMp1803970)

ለህክምና ተማሪና ባለሞያ ይሄንን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ቢሆንም የአእምሮ ጤና እጅግ ወሳኝ ነው። የህክምና ግቢዎችም በዚህ ላይ ያላቸውን አቋም ሊፈትሹና ሊያሻሽሉ ይገባል። የምክር አገልግሎቶች መጠናከር አለባቸው፣ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች በብዛት መዘጋጀት አለባቸው። የህክምና ግቢዎች ስለ ተማሪዎቻቸው ጤና ሊያሳስባቸው ይገባል። ለተማሪዎች የአእምሮ ጤና የሚሰጡት ትኩረትና ያላቸው አቋም ወደፊት ሊያፈሯቸው ስለሚፈልጉት ዶክተሮችና የጤና ባለሞያዎች ብዙ ነገር ስለሚናገር ማለት ነው።

 

References

  1. World Health Organization Official website – who.int
  2. Ourworldindata.org
  3. The New England Journal of Medicine – nejm.org
  4. American Psychiatry Association
  5. [1]https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/mental-disorders#:~:text=In%202019%2C%201%20in%20every,of%20the%20COVID%2D19%20pandemic
  6. [2]https://ourworldindata.org/mental-health#:~:text=Mental%20and%20substance%20use%20disorders%20are%20common%20globally,mental%20or%20substance%20use%20disorders.
  7. [3]https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/mental-disorders#:~:text=In%202019%2C%201%20in%20every,of%20the%20COVID%2D19%20pandemic.
  8. [4] American Psychiatric Association – https://www.psychiatry.org