የአጥንት መሳሳት (osteoporosis) ምንድነው?

በ – ቤተልሔም ታደለ-  5ተኛ አመት የህክምና ተማሪ (በቅ/////)

አርትኦት እና እርማት – ዶ/ር ኤዶም ገብረመድህን (Assistant Professor of Internal medicine at Dilla University College of Medicine and Health Scinces )

የአጥንት መሳሳት (osteoporosis) ምንድነው?

የአጥንት መሳሳት በሽታ (ኦስቲዮፖሮሲስ) በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙት አጥንቶች በተለያዩ ምክንያቶች ክብደት፣ ጥንካሬ ወይም ይዘታቸውን አጥተው ልፍስፍስ በመሆን ለስብራት ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ ህመም ሲሆን ብዙ ጊዜ ምልክት ሳያሳይ የሚቆይ የተለመደ የአጥንት በሽታ ነው። 

በሁለቱም ጾታዎች፣ በሁሉም ዘሮች እና በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሚከሰት ቢሆንም፣ ከድህረ ማረጥ በኋላ ባሉት ሴቶች፣ ትንሽ የአጥንት መዋቅር ባላቸው ሰዎች፣ በአረጋውያን እና በነጮች/ እስያውያን ውስጥ በጣም በተደጋጋሚ በመከሰት ይታወቃል።

ይህ በሽታ በአነስተኛ የአጥንት ክብደትና በአጥንት ሕብረ ሕዋስ አወቃቀር መበላሸት ይታወቃል። በዚህም ምክንያት የአጥንት ስብራትን ያስከትላል።

ለአጥንት መሳሳት በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው?

ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ የተደረጉ ጥናቶች የአጥንት መሳሳት በሽታ በዋነኝነት ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ህመም እንደሆነና በጊዜ ከታወቀ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ሊታከም የሚችል በሽታ እንደሆነ ያሳያሉ።

የሚከተሉት ሁኔታዎች አንድን ሰው በከፍተኛ ደረጃ ለአጥንት መሳሳት እንዲጋለጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።

 –ድህረ ማረጥ ላይ ያለች ሴት (45 አመት በላይ የሆነች ወይም የወር አበባ ማየት ያቆመች)

 –60 አመት እድሜ በላይ መሆን

ሲጋራ ማጨስ

አልኮሆል መጠጣት

የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ

-የቫይታሚን ዲ እና ካልሲየም እጥረት

ለረጅም ጊዜ መድሀኒቶችን መውሰድ ለምሳሌ እስቴሮይዶች፣ የደም ማቅጠኛ እንክብሎች፣ የካንሰር መድሀኒቶች (በጎንዮሽ ጉዳት አማካኝነት)

ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ በሆርሞን መዛባት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎች (እንደ ኩሺንግ ሲንድሮም፣ የታይሮይድና ፓራታይሮይድ ሆርሞን መዛባት ወዘተ) እና የካንሰር ህመም አይነቶች ለአጥንት መሳሳት በሽታ ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡

ህመሙ ምን ምን ምልክቶች ሊኖሩት ይችላሉ?

የአጥንት መሳሳት በሽታ በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ስብራት ከማምጣቱ በፊት ምልክት ስለማያሳይ ለህመሙ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የቅድሚያ ምርመራ ማድረግና ተገቢውን ህክምና መጀመር ብዙውን ጊዜ በቂ ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። የአጥንት መሳሳት ባለባቸው ታካሚዎች ላይ በትንሽ ግጭት ወይም ከአጭር ከፍታ ላይ የመውደቅ አደጋን ተከትሎ የአጥንት ስብራት ሊከሰት ይችላል። ይህም በቶሎ የህክምና እርዳታ ካልተደረገለት ውስብስብ የጤና ችግሮችን በማምጣት እንደ መጉበጥ፣ ተደጋጋሚ ስብራት፣ ለረጅም ጊዜ የቆየ የአጥንት ህመምና የቁመት ማጠርን ብሎም የአቋም መዛነፍን ሊያስከትል ይችላል።

በበሽታው ምክንያት በዳሌ/በወገብ አጥንት፣ በእጅ አንጓ መገጣጠሚያ አጥንቶች እንዲሁም በአከርካሪ አጥንት ላይ ስብራት ሊከሰት ይችላል።  ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የአከርካሪ አጥንት ስብራቶች ህመምአልባ ቢሆኑም ታካሚዎቹ ግን የተጣመመ አቋም ወይም የቁመት ማጠር አጋጥሟቸው የህክምና እርዳታ ሲጠይቁ ሊስተዋሉ ይችላሉ።

ምርመራ አለው?

አዎ! አንድ ሰው የአጥንት መሳሳት ይኑርበት አይኑርበት ለማወቅ ወደ ሆስፒታል በመሄድ በሀኪም እርዳታ ቅድመምርመራ በማድረግ የአጥንቱን (ጥንካሬ) የጤና ሁኔታ ማወቅ ይችላል።

በአጥንት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን የጥግግት መጠን  ለማወቅ Dual energy Xray Absorptiometry (DXA) የሚባል የተለየ አይነት የራጅ ምርመራ ማድረግ ለአጥንት መሳሳት በሽታ ተጋላጭ ለሆኑ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶችና ወንዶች ይመከራል። በተለይም:- 

* ትንሽ ግጭት ወይም ከአጭር ከፍታ ላይ የመውደቅ አደጋን ተከትሎ የተከሰተ የአጥንት ስብራት ካጋጠማቸው

20 ዓመታቸው ከተመዘገበው ከከፍተኛው ቁመት 4 . ወይም ከዚያ በላይ ቁመት መቀነስ ካለ 

* ቀደም ሲል ከተመዘገበው የቁመት ልኬት በኋላ 2 .. ወይም ከዚያ በላይ ቁመት መቀነስ

* የቅርብ ጊዜ ወይም የረጅም ጊዜ የግሉኮኮርቲኮይድ /ስቴሮይድ ሕክምና የሚወስዱ ከሆኑ ናቸው።

ሕክምና አለው?

አዎ! አንድ ሰው የአጥንት መሳሳት እንዳለበት በሀኪም ከተረጋገጠ መድሀኒት ታዞለት በመውሰድ መታከም ይችላል። ነገር ግን ህክምናው ቀድሞ የተፈጠረውን የአጥንት መሳሳት ለመመለስ ሳይሆን ወደፊት ሊፈጠር የሚችለውን ለማስቆምና ለመግታት የሚረዳ ነው።

በመሆኑም እርስዎ እድሜዎ 60 ከዛ በላይ ከሆነ  ዛሬውኑ ወደጤና ተቋም በመሄድ የአጥንት ምርመራና ክትትልዎን ይጀምሩ።

የአጥንት መሳሳትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

አንድ ሰው የአጥንት መሳሳት በሽታ እንዳይዘው ለመከላከል በዋናነት አመጋገቡን ማስተካከል አስፈላጊ ነው። ይኸውም በቫይታሚን ዲና በካልሲየም የበለፀጉ ምግቦችን ለምሳሌ ወተትና የወተት ተዋፅዖዎች፣ ጭማቂ፣ የተፈጨ አጃ፣ ዓሳ/ የዓሳ ዘይት፣ሰርዲን፣ ባቄላና የመሳሰሉትን አዘውትሮ መጠቀም ይመከራል ።

በተጨማሪም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር ሲጋራ አለማጨስና ከአልኮል መጠጥ ነፃ በመሆን መከላከል ይቻላል።

 

References:

  1. World Health Organization (WHO). WHO scientific group on the assessment of osteoporosis at primary health care level: summary meeting report. Available at: https://www.who.int/chp/topics/Osteoporosis.pdf.
  2. Uptodate
  3. https://www.amboss.com/us/knowledge/Osteoporosis 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg