የኩላሊት ንቅለ ተከላ

By: Befekadu Molalegn Abebe(GP)

ፍቃዱ ሞላልኝ (ጠቅላላ ሀኪም)

Reviewed/Approved  by: Dr. Fitsum Tilahun (Editor at Yetena Weg/ Nephrologist)

 

የሰውነታችን ኩላሊቶች ሥራ ሲያቆሙና መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ካሉት የህክምና አማራጮች አንዱ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ነው። የኩላሊት ንቅለ ተከላው በሕይወት ካለ የቅርብ ዘመድ ወይም ጓደኛ ለታማሚው ሊሰጥ ይችላል። ባደጉ አገራት ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎችም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ይደረጋል።  

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከኩላሊት እጥበት በተሻለ መልኩ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግልና የኩላሊት ታማሚን የህይወት አኗኗር በይበልጥ የሚጠቅም የህክምና መንገድ ነው።

ታድያ የኩላሊት ታማሚዎች በኩላሊት እጥበት ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ከሚጨርሱ ለምን ንቅለተከላ አድርገው አይገላገሉም??

ምንም እንኳን የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከኩላሊት እጥበት አንፃር ሲታይ ዘላቂ መፍትሄ ቢመስልም እንደልብ ለሁሉም የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት ታማሚዎች አይደረግም። ምክንያቱም

  • የአቅርቦት ችግር 
  1.  የአገልግሎት እንደ ልብ አለመኖር 
  2. ኩላሊት የሚለግስ ሰው አለመኖር 
  • የታማሚው ለሕክምናው ብቁ ሆኖ አለመገኘት 
  1. በሰውነት የተሰራጨ ከፍተኛ የሆነ ኢንፌክሽን
  2. በህክምና ቁጥጥር ስር ያልሆነ ካንሰር
  3. በህክምና ቁጥጥር ስር ያልሆነ የአእምሮ ህመም
  4. የታወቀ የአደንዛዥ መድሃኒት ጥገኝነት
  5. የታወቀና ቀሪ የህይወት ጊዜን በእጅጉ የሚያሳጥር ማንኛውም አይነት ህመም
  6. የታካሚው ሰውነት ከሰጪው የሚመጣውን የአካል ክፍል እንደማይቀበል በቅድመ ምርመራ ሲረጋገጥ
  • ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪ ታማሚውን በተለይ ለኩላሊት ንቅለተከላ ብቁ የማያደርጉ ምክንያቶች ሲገኙ። እነዚህም
  1. ያልታከመ የሄፕታይተስ ቢ ወይም ሲ ቫይረስ በደሙ መኖር
  2. ከፍተኛ ውፍረት
  3.  የካንሰር ታማሚ ከሆኑ( ከካንሰር ነፃ ከሆኑ 2-5  አመት በኋላ ማድረግ ይችላል)
  4. የታካሚውና የኩላሊት ለጋሹ የደም አይነት መለያየት

የኩላሊት ንቅለተከላው ከመደረጉ በፊት ምን መታወቅ አለበት?

  1. የኩላሊት ታካሚው ሰውነት አዲስ የሚመጣውን ኩላሊት የመቀበል አቅም በቅድመ ንቅለተከላ ምርመራ መረጋገጥ አለበት።
  2. የኩላሊት ለጋሹ መሉ ጤንነት ማለትም ተላላፊ ከሆኑም ሆነ ካልሆኑ እንዲሁም ንቅለተከላው ከተካሄደ በኋላ የታካሚውን ጤናና ህይወት ሊያውኩ ከሚችሉ ማንኛውም አይነት ህመሞች ነፃ መሆኑ በቅድመ ንቅለተከላ ምርመራ መረጋገጥ አለበት።
  3. ታካሚው ከላይ ከተዘረዘሩትና ለኩላሊት ንቅለተከላ ብቁ እንዳይሆን ሊያደርጉት ከሚችሉ ሁኔታዎች ነፃ መሆኑ መረጋገጥ አለበት።

የኩላሊት ልገሳው ከማን ቢሆን ይመረጣል?

የኩላሊት ልገሳው በህይወት ካለም ከሌለም ሰው ሊደረግ የሚችል ሲሆን በህይወት ካለ ሰው በተለይ ደግሞ የቅርብ የቤተሰብ አባል ቢሆን የንቅለተከላው ስኬታማነት ይጨምራል። ነገር ግን በቅድመ ንቅለተከላው ምርመራ ወቅት በኩላሊት ለጋሽና በታካሚው የሰውነት ህዋሳት መካከል አለመጣጣም መኖሩ ቢረጋገጥ ንቅለተከላው ስኬታማ የመሆን እድሉን በእጅጉ ስለሚቀንስ ንቅለተከላው አይደረግም።

በሌላ በኩል በህይወት ከሌለ ሰው ላይ የሚወሰድ ኩላሊትን እስከ 48ሰአት ድረስ በማቀዝቀዣ ውስጥ በማቆየት ቅድመ ንቅለተከላ ምርመራው ከታለፈ በኋላ ለታካሚው መለገስ ይቻላል።  

በኩላሊት ንቅለተከላ ወቅት የሚደረጉ ዝግጅቶች

የኩላሊት ንቅለተከላ ምንም እንኳን ቅድመ ንቅለተከላ ምርመራዎች ከታለፉ በኋላ የሚደረግ ቢሆንም አዲስ የሰውነት ክፍል እንደመሆኑ መጠን ከተቀባዩ ሰውነት ጋር አለመጣጣም ሊኖር ይችላል። ይህ ደግሞ ህክምናውን መሉ በሙሉ ሊያፈርሰው ስለሚችል በዋነኝነት የሚሰጠው ህክምና የታካሚውን የነጭ ደም ሴሎች በቁጥርም በብቃትም እንዲደክሙና አዲስ የሚመጣውን የሰውነት ክፍል እንደ ባእድ አይተው ምላሽ እንዳይሰጡ የማድረግ ህክምና ይሰጣል። ይህ ግን በሌላ ጎኑ ታካሚውን ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ የሚያደርግ ቢሆንም የኩላሊት ንቅለ ተከላው ባይካሄድ ሊከተል ከሚችለው ጉዳት ጋር በማመዛዘንና ሌላ የተሻለ አማራጭ መኖር አለመኖሩን በማጤን በሀኪሙና በታካሚው የጋራ ስምምነት የሚደረግ ነው።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

EMSA Digital Library

online platform where you can find resources

Fellowship Opportunities

International Opportunities For Young Leaders

ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ድንገተኛ እርዳታ ካስፈለግዎ

በነዚህ ቁጥሮች እርዳታ ያግኙ

Subscribe