ዲያሊስስ ወይስ ንቅለተከላ

በተስፋዬ ብርሃኑ
ጎንደር ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኢንተርን ሐኪም

 

መግቢያ

በ2017 ጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ጥናት መሠረት 700 ሚሊዮን ያህሉ የዓለም ሕዝብ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ሕሙም ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጋው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ከ90% በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሕክምና እያገኙ አለመሆናቸው ችግሩን ያከፋዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ እና በሆኑ በሽታዎች ድርብ ጫና እያሰተናገደች ትገኛለች፡፡ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች አንዱ ሲሆን ለኩላሊት መድከም በማጋለጥ ለሥቃይና ሞት እየዳረገ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ የጤና ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ ደካማ በመሆኑ ምክንያት በመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት በሽታ የተጠቁ፣ በኩላሊት እጥበት ላይ ያሉ፣ ለንቅለተከላ ወረፋ በመጠበቅ ላይ ያሉ፣ እንዲሁም ሕይወታቸው ያለፈ የሥርጭትና የክስተት መጠን በጥናት ባይሰፍርም የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ቤት ያንኳኳ ስለመሆኑ ግን ነጋሪ አያሻውም፡፡

ኩላሊት ደምን በማጣራት ቆሻሻን፣ ከመጠን ያለፈ ጨውንና ውሃን ታስወግዳለች፡፡ ኩላሊት ይህን ተግባሯን ለ3ወር እና በላይ ያህል ስትተወው ወይም በመጠን ቀንሳ ስትገኝ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ አለ እንላለን፡፡ በሽታው 5 ደረጃዎች ሲኖሩት እስከ ደረጃ 3 ድረስ ምልክት አልባ ሊሆን ይችላል ይህም ኩላሊት ከግማሽ ያህል ክፍሏ በላይ እንኳ እስኪጎዳ ድረስ ተግባሯን መቀጠል ስለምትችል ነው፡፡ ደረጃ 4 እና 5 ላይ የኩላሊት የማጣራት አቅም ክፉኛ ስለሚጎዳ ትርፍ ፈሳሽ፣ ንጥረነገሮችና መርዛማ ጽዳጅ ውህዶች በሰውነታችን ይከማቻሉ፡፡ በዚህ የተነሣ የተለያዩ ምልክቶች(ትንፋሽ ማጠር፣ ድካም ስሜት…) ይታያሉ፡፡ ይህ ሳይስተካከል ቀርቶ ሙሉ በሙሉ ሥራዋን ካቆመች ኩላሊት ደክማለች(የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት በሽታ ወይም ደረጃ 5) ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ በሕይወት ለመቆየት የኩላሊት ምትክ ሕክምና ማለትም የኩላሊት እጥበት ወይም ንቅለ
ተከላ ያስፈልጋል፡፡

 

የኩላሊት ምትክ ሕክምና ለመጀመር የሚያስችሉ አመላካቾች፦

  • የዩሬምያ ምልክቶች(ድካም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የክብደት መቀነስ፣ ማስመለስ፣
    ማቅለሽለሽ)
  • የፈሳሽ መጠራቀም
  • የንጥረነገር መዛባት(ፖታስየም፣ ፎስፈረስ፣ ካልስየም፣ አሲድ)

 

የኩላሊት እጥበት – Dialysis

ሰው ሰራሽ ኩላሊት ሲሆን ከሆርሞን ማምረትና አንዳንድ ተግባራት ውጭ የተከማቸ ፈሳሽን፣ ናይትሮጅን ነክ መርዛማ ውህድን እንዲሁም የበዙ ንጥረነገሮችን ከሰውነታችን በማስወገድ የተጣራ ደምን ወደ ሰውነታችን መልሶ ያስገባል፡፡

 

የደም ሥር እና የሆድ እቃ(Peritoneal dialysis) በመባል በ2 ይከፈላል፡፡ (በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ስለሚሰጠው የደም ሥር (Hemodialysis) እንመለከታለን) በደም ሥር የሚደረገው ዲያሊስስ በሳምንት 3 ጊዜ ሲሰጥ እያንዳንዳቸው ከ3-5 ሰዓት ያህል ሊፈጁ ይችላሉ፡፡

 

የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልገው መቼ ነው?

  • ዲያሊስስ በደረጃ 5 የኩላሊት በሽታ ተጠቅተን ከላይ የጠቀስናቸው አመላካቾች ሲኖሩ ብቻ ሳይሆን አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት(AKI) ሲገጥመን ለምሳሌ መድኃኒቶችን ከመጠን በላይ ወስደን ስንጎዳ፣ እባብ ነድፎን ኩላሊታችን በመርዙ ክፉኛ ሲጎዳ፣ በተለያየ ምክንያት መርዝ
    ጠጥተን ሰውነታችን ሲቆጣ፣ በጸና ታመን ወይም በተለያየ የጤና እክል ምክንያት ወደ ኩላሊታችን የሚሄደው ደም ቀንሶ ኩላሊታችን ሲጎዳ እና ኩላሊት ተግባሯን ባለመከወኗ ምክንያት መርዛማ የአጸግብሮት ውጤቶች ተጠራቅመው፣ ፈሳሽ በዝቶ ሕይወታችን አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የደም ምርመራ ውጤቶች አመላካች ሲሆኑ የዲያሊስስ እርዳታ በጊዜያዊነት ሊያስፈልገን ይችላል፡፡

 

የጎንዮሽ ጉዳት

አብዛኛው ሰው ዲያሊስሱን በስኬት ቢጨርስም አንዳንዴ የጎንዮሽ ጉዳት ሊከሰት ይችላል፡፡ የደም ግፊት መውረድ፣ ራስ የመቅለል ስሜት፣ ቃታ መንሣት፣ የሆድና ጡንቻ ሕመም፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ከክስተቶቹ መካከል ሲሆኑ በባለሙያ ክትትል እንዳይፈጠሩ ወይም ከተከሰቱ
እንዲስተካከሉ ማድረግ ይቻላል፡፡

 

ዲያሊስስ ላይ ያለ ሰው ምን ጥንቃቄ ያድርግ?

  1. የምግብ ማስተካከያ ማድረግ (የሥነ ምግብ ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል)
    • የጨው፣ ፖታስየም (ዶሮ፣ እንቁላል፣ ለውዝ፣ አፕል፣ የበሰለ ጎመን፣ ካሮት፣ቀይ ሽንኩርት) እና ፎስፈረስ መጠናቸው አናሳ የሆኑ ምግቦችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
    • የውሃ(የፈሳሽ) መጠናቸውን መገደብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ብጠማ ምን ላድርግ፦
      ☞ አፍን መጉመጥመጥ ግን አለመዋጥ፣
      ☞ ማስቲካ ማኘክ ወይም ደረቅ ከረሜላ መምጠጥ፣
      ☞ በረዶ መምጠጥ (ዘግይቶ ስለሚያልቅ)
  2. ለተሰራው ደም ሥር ጥንቃቄ ማድረግ
    • በሳሙናና ለብ ባለ ውሃ በየቀኑ እንዲሁም ከዲያሊስስ በፊት ማጠብ
    • አካባቢውን አለማከክ
    • የኢንፌክሽን ምልክቶችን ማወቅ (ሙቀት፣ መቅላት፣ ማበጥ)
    • ንዝረታዊ የደም ፍሰት መኖሩን ማረጋገጥ
    • የደም ሥር ማገናኛ (Vascular access) ለሚገኝበት ክንድ ጥንቃቄ ማድረግ (ጥብቅ ያለ ልብስ፣ ጌጣጌጥ አለመጠቀም፣ አለመንተራስ፣ ከባድ እቃ አለማንሣት፣ የደም ግፊት መለካትና ናሙና መውሰድ አይፈቀድም፡፡ )
  3. ክብደት መለካት (በየቀኑ)
  4. የደም ምርመራ (ክሪያቲኒን፣ ኤሌክትሮላይት) ማድረግ

 

የኩላሊት እጥበት ፍቱን ነውን?

አይደለም፡፡ ደረጃ 5 የኩላሊት ሕሙማን ለንቅለተከላ ብቁ ካልሆኑ በስተቀር በጊዜያዊነት የሚሰጥ ሕክምና ነው፡፡

 

ንቅለ ተከላ ምንድነው?

ንቅለ ተከላ አዲስና ጤነኛ ኩላሊት የደከመ ኩላሊት ላለው ሰው የሚሰጥበት ቀዶ ሕክምና ነው፡፡ (ሰው ለመኖር አንድ ኩላሊት ብቻ ይበቃዋል፡፡ ) በሕይወት ካለ ሰው ወይም ተናዞ ከሞተ ሰው ኩላሊት ሊገኝ ይችላል፡፡ በሕይወት ካለ ሰው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማከናወን ተመራጭ መሆኑን ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡

 

ንቅለ ተከላ የተከለከለባቸው ሁኔታዎች

  • የከፋ የልብ በሽታ
  • ካንሰር
  • ከልክ ያለፈ ውፍረት
  • ከቀዶ ሕክምናው በኀላ በየቀኑ መድኃኒት መውሰድ አለመቻል(የአእምሮ ሕሙም)

 

ኩላሊት መለገስ የሚችለው ማነው?

ኩላሊት ለመለገስ ጤነኛ እና ከ18 ዓመት በላይ ከመሆን ባለፈ መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና ምርመራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኩላሊትን ለጉዳት የሚዳርጉ የጤና እክሎች ማለትም ከቁጥጥር ከወጣ ስኳር፣ ደምግፊት፣ ውፍረት እና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ነጻ መሆን አለበት፡፡

 

ኩላሊት የለገሰ ሰው ለኩላሊት መድከም በሽታ ተጋላጭነቱ ምን ያህል ነው?

ለጋሾች ከጠቅላላው ሕዝብ የበለጠ ጤናማ በመሆናቸው የተነሣ ለኩላሊት መድከም በሽታ ያላቸው ተጋላጭነት ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የእድሜ ጣሪያቸው ከጠቅላላው ማኅበረሰብ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም መደበኛ የሆነ የጤና ክትትል እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ከንቅለተከላው ጋር
ተያይዞ የሚከሰት የቀዶ ሕክምና የጤና እክል ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር የለጋሹ የሕሊና እርካታና የተቀባዩ ወደ ጤንነት መመለስ የንቅለ ተከላ ሕክምናን ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ምስል 1 ፡ የዲያሊስስ እና ንቅለተከላ ጥቅም ንጽጽር

 

በዋጋም ሆነ በአቅርቦት ወደማይደፈሩት በኢትዮጵያ እምብዛም ወደ ማይገኙት የሕክምና አማራጮች ከመግባቴ በፊት ሥር ለሰደደ የኩላሊት በሽታ ተጋላጭነቴን ብቀንስስ… ቢኖርብኝ እንኳ ውስብስብ የጤና እክሎችን ሳያመጣብኝ በፊት እኒህን ባደርግስ?

  • በዓመት ወይም በ2ዓመት እንደአስፈላጊነቱ የደም፣ የሽንትና የሆድ አልትራሳውንድ ብታይ
  • የሥኳሬን መጠን ብቆጣጠር
  • የደም ግፊቴን ባስተካክል
  • ተደጋጋሚ የሽንተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኔን ብታከም
  • የሰውነት እንቅስቃሴ ባደርግ (በሳምንት ቢያንስ ለ150 ደቂቃ)
  • ሲጋራ ብተው
  • ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ የሚሸጡ መድኃኒቶችን በጥንቃቄ ብጠቀም(የሕመም ማስታገሻና ሌሎችንም)
  • ጭንቀት ብቀንስ
  • አኗኗሬንና አመጋገቤን ባስተካክል
  • የሉፐስ ምርመራ ባደርግስ
  • ከቤተሰቤ አንዳቸው የኩላሊት ሕሙም ከሆኑ ለራሴም ብመረመርስ

 

ማጠቃለያ

ለኩላሊት መድከም ዋነኛ ምክንያት ወይም አባባሽ የሆኑ ነገርግን ማስተካከል የምንችላቸው ለምሳሌ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ትምባሆ ማጨስ፣ ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት እና ሌሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የኩላሊታችንን ጤና መጠበቅ እንችላለን፡፡ የሆነው ሆኖ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ምልክቶችን ማስተዋል ከጀመርን ቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ብንመረመር እና ብንታከም፣ የኩላሊት ምትክ ሕክምና አማራጮች ላይ ከሐኪም ጋር ውይይት ብናደርግ ካላስፈላጊ ወጪ፣ የሥነልቦና ጫና እና ውስብስብ የጤና መቃወስ ራሳችንን እናድናለን፡፡

 

ዋቢዎች

  1. UpToDate.2022
  2. www.hopkinsmedicine.org/transplant
  3. Tuso PJ. SERVE Ethiopia. Perm J. 2009 Summer;13(3):51-64. doi: 10.7812/TPP/08-082. PMID: 20740090; PMCID: PMC2911814.
  4. www.whhs.com\chronic kidney disease FAQ
  5. American Journal of Transplantation 2013; 13: 111–118 Wiley Periodicals Inc.
  6. John Wiley & Sons A/S. Published by John Wiley & Sons Ltd Pediatric Transplantation DOI: 10.1111/petr.12238